በዓለማችን በየዓመቱ ከ 15 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ከመወለጃ ቀናቸው አስቀድመው እንደሚወለዱ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያም በዓመት የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር 400 ሺህ እንደሚደርስ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የመወለጃ ቀናቸዉ ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት የሚባሉት የእርግዝና 37ኛ ሳምንት ከመጠናቀቁ በፊት የሚወለዱ ናቸዉ።
እነዚህ ከመወለጃ ቀናቸው አስቀድመው የሚወለዱ ህፃናት ለተለያዩ ህመሞች በቀላሉ ተጋላጭ ከመሆናቸውም በላይ በርካቶቹ 1 ወር ሳይሞላቸው ለህልፈት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የመደበኛ እርግዝና ርዝማኔ ከ 37 እስከ 42 ሳምንታት ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተወለደ ሕፃን በመደበኛው የመውለጃ ጊዜ የተወለደ ሕፃን ይባላል፡፡
በኢትዮጵያ ከ10 በህይወት ከሚወለዱ ህጻናት አንዱ የመወለጃ ቀኑ ሳይደርስ እንደሚወለድም በቅርብ ዓመት የወጡ ጥናቶች ያመላክታሉ።
የመወለጃ ቀናቸዉ ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት አጋጣሚ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች መንስኤው በትክክል ባይታወቅም ለዚህ ክስተት የሚያጋልጡ ምክንያቶች እንዳሉ ግን ይነገራል፡፡
በእርግዝና ወቅት እንደ በእናቶች ላይ እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ እና ኢንፌክሽኖች ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ያለጊዜው መወለድ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሲሆን ማጨስ፣ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም እና በቂ ያልሆነ የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ ለችግሩ የሚያጋልጡ ሌሎች ምክንያት ናቸው፡፡
የመወለጃ ቀናቸዉ ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት ተገቢዉን እንክብካቤ ካገኙ ጤናማ ሆነዉ እንደሚያድጉም የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለዚህም በቂ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ እና ወላጆች ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸው ይገለፃል።
በትዝታ ተሰማ
#ebc #ebcdotstream #preterm_birth