Search

አዲስ አበባ የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ የማድረግ ተግባራችን ጣፋጭ ፍሬ እያፈራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ቅዳሜ የካቲት 21, 2018 153

የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ለከፋ ማኅበራዊ ችግር ተጋልጠው ይኖሩ የነበሩ 909 ሴቶችን ዛሬ በ4ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሠልጥኖ በማስመረቅ ወደ ሥራ ማሰማራቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ተመራቂ ሴቶቹ ቀን ጨልሞባቸው፣ ተስፋ ቆርጠው እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር በሰደዱ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች እና ድርጊቶች ሰብዓዊ ክብራቸውን ተነጥቀው ይኖሩ እንደበር ከንቲባዋ አንሥተዋል።
በሰው ሕይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ የማድረግ ተግባራችን ጣፋጭ ፍሬ እያፈራ ነው፤ ለዚህም አንዱ ማሳያ የለነገዋ የሴቶች ማዕከል ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነው ተስፋ ለቆረጡ እህቶቻችን አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መክፈቻ ሆኗል።
ትላንት በጎዳና፣ በችግር እና በተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶች ዛሬ ራሳቸውን ችለው ለተሻለ ሕይወት እንዲበቁ እያስቻለ ያለ እውነተኛ የተስፋ ማዕከል ነው።
እስከዛሬ ማዕከሉ በድምሩ 2 ሺህ 401 ሠልጣኞችን አስመርቆ ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩ እና ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆኑ ማስቻሉን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
የእነዚህ የእህቶቻችን እና የልጆቻችን ሕይወት ከጨለማ ወጥቶ፣ ወደ ማዕከሉ ሲመጡ የነበራቸው መልክ ተቀይሮ፣ በባህሪ ታንጸው፣ በዕውቀት እና በክህሎት ታጥቀው ወደ ብሩህ ነገ ሲሸጋገሩ ማየታችን የላቀ ደስታን ይሠጠናል ነው ያሉት።
“ውድ የዘንድሮ ተመራቂዎች፤ በቆይታችሁ ካለፋችሁበት መራራ ሕይወት ለመውጣት ባሳያችሁት ቁርጠኝነት እና ከፍተኛ ትጋት እንዲሁም ባሳያችሁት ፈጣን ለውጥ እጅጉን እንኮራለን” ሲሉም አበረታትዋል።
“በሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና (COC) 97.5% ማስመዝገባችሁ የብቃታችሁና የትጋታችሁ ትልቅ ማሳያ ነው። ይህም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ዕድሉ ከተመቻቸላቸው፣ ትንሽ ፍቅርና ድጋፍ ካገኙ ለችግር የማይበገሩ እና ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ ነው” በማለት አክለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው፣ ለማዕከሉ አመራሮች፣ ለቦርድ አባላት እና ለበጎ ፈቃደኞች ለነበራቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።