የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ በተካሄደው "የወደፊት ቴክኖሎጂዎች ፎረም" ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የወደፊቱ ቴክኖሎጂዎች ለሁሉም እንጂ ለጥቂቶች ብቻ መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡
ሀገራቸው በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያላትን እውቀት የሰው ልጆችን በሚጠቅም መልኩ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ረገድ ባዮቴክኖሎጂና ጄኔቲክስ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ወሳኝ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የባዮ ኢኮኖሚ ከሳይንሳዊ እውቀት ባለፈ አዲስ የኢንዱስትሪ ዘይቤን እየፈጠረ መሆኑንና የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል እንዲሁም ሥነ-ምህዳርን ለመጠበቅ ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።
የወደፊት ቴክኖሎጂዎችን በእኩልነት ማግኘት ለሥልጣኔ ፍትሐዊ ዕድገት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ እነዚህ ዕድሎች የጥቂት ወገኖች ብቻ መሆን እንደሌለባቸው አሳስበዋል።
ሩሲያ በዘርፉ ያላትን ልምድና እውቀት ለሰው ልጅ ጥቅም ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም ነው ፕሬዝዳንቱ የጠቆሙት።
በተለይም በብሪክስ እና በሌሎች ማኅበራት አማካኝነት በባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ የጋራ ሳይንሳዊ፣ ትምህርታዊና የኢንቨስትመንት መርሃ ግብሮችን ለመተግበር ሩሲያ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
ዲጂታል ፕላትፎርሞችና ሰው ሰራሽ አስተውሎት በባዮቴክኖሎጂ ጋር ተዳምረው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱም ፕሬዝዳንቱ መግለፃቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
#EBC #Russia #BRICS #TechnologyJustice #GlobalEquality #FutureTech #Innovation