በአሁኑ ዘመን "ውኃ ቀጣዩ የዓለም ግጭት መንሥኤ ይሆናል" የሚሉ ሥጋቶች እየበረቱ ናቸው።
ቱርክዬ ግን ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ብሔራዊ ጥንካሬ እና የዲፕሎማሲ የበላይነት የቀየረችበት መንገድ ትልቅ ማስተማሪያ ነው።
በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ ላይ የገነባችው ስትራቴጂካዊ መዋቅር፣ የውኃ አስተዳደር ከቴክኒካዊ ጉዳይ ባለፈ የጥበብ እና የሰላም መንገድ መሆኑን ያሳያል።
የቱርክዬን የውኃ ዲፕሎማሲ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የቱርክዬ መርሕ "ፖለቲካ ያላገደው የጋራ ተጠቃሚነት" ነው። ለዚህም "የአርፓቻይ ተአምር" ተብሎ የሚታወቀው የቱርክዬ እና አርሜኒያ ግንኙነት ዋነኛ ማሳያ ነው። ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖራቸውም እንኳ፣ በድንበራቸው ላይ ያለውን የአርፓቻይ ግድብ በጋራ ያስተዳድራሉ።

የፖለቲካ ልዩነት የጋራ የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠቀም ሊያግደን አይገባም በሚል መርሕ፣ ውኃውን እኩል በመካፈል ለዘመናት ያለምንም ግጭት ለልማት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ይህ ተግባር "ውኃ ከፖለቲካ በላይ ነው" የሚለውን እሳቤ በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ቱርክዬ ከቡልጋሪያ እና ግሪክ ጋር በሜሪች (Maritsa) ወንዝ ላይ ያላት ልምድ ሌላው የመልካም ጎረቤትነት አብነት ነው። ከቡልጋሪያ ጋር በመተባበር የወንዙ ሙላት ሲጨምር መረጃ የሚለዋወጡበት "የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት" ዘርግተዋል። ይህ በሳይንስ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ትብብር፣ በድንበር አካባቢ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ እና የንብረት ጥፋት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንስዋል። ይህም ግልጽ የመረጃ ልውውጥ (Data Sharing) በመንግሥታት መካከል መተማመንን ለመፍጠር ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ያሳያል።

ቱርክዬ ግድቦችን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንደ ዋስትና የመጠቀም ስልትንም ትከተላለች። በኤፍራጥስ እና ጤግሮስ ወንዞች ላይ ግዙፍ ግድቦችን ስትገነባ፣ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሶርያ እና ኢራቅ በውኃ እጥረት እንዳይጎዱ ኃላፊነት የተሞላበት ዋስትና ሰጥታለች። ግድብ ውኃን መቆጣጠሪያ ብቻ ሳይሆን፣ ወጥነት ያለው የውኃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ድርቅን ለመከላከል የሚያስችል መሣሪያ መሆኑን በተግባር አሳይታለች።
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ሊፈታ የሚገባው በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ብቻ እንደሆነ ስለምታምን፣ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን ውድቅ በማድረግ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ታተኩራለች።
የቱርክዬ ልምድ ከኢትዮጵያ እና ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር ያለው ቁርኝት
ይህ ስትራቴጂ ከኢትዮጵያ እውነታ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው። ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ 85 በመቶ ምንጭ ብትሆንም፣ ለዘመናት በቅኝ ግዛት ውሎች እና በግብፅ የዲፕሎማሲ ጫና ምክንያት በሀብቷ እንዳትጠቀም ተደርጋ ቆይታለች።
ግብፅ የውኃ ጉዳይን በተደጋጋሚ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በማቅረብ ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ብትሞክርም፣ ኢትዮጵያ ግን እንደ ቱርክዬ ሁሉ "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሔ" በሚል መርሕ ጫናዎችን በመመከት የታሪክ መጋረጃውን ቀድዳለች።
ዛሬ ላይ የቱርክዬን ፈለግ በመከተል በጽናት የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የበላይነትን አጎናጽፏታል። "የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት" (CFA) ወደ ተፈጻሚነት መሸጋገሩም፣ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የማልማት መብታቸውን ከታችኞቹ ሀገራት "ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስባቸው" የማድረግ ኃላፊነት ጋር አጣጥመው ለመጓዝ መወሰናቸውን ያሳያል። የቱርክዬ ተሞክሮ እንደሚያስተምረን፣ ውኃ የጦርነት ቀስቃሽ ሳይሆን በሳይንሳዊ መረጃ እና በሁለትዮሽ መተማመን ላይ የተመሠረተ የሰላም ድልድይ ሊሆን ይችላል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Turkiye #diplomacy