ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ የ“ሆራይዘን” ድንበር ተሻጋሪ የፋይበር መስመር ዝርጋታን እውን ለማድረግ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት በጅቡቲ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት ከፍተኛ አቅም ያለው የኦፕቲካል ፋይበር መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የጅቡቲን የባሕር ውስጥ የፋይበር ኬብሎች በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ከሱዳን ጋር የሚያስተሳስር ነው፡፡
ይህም ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የኢንተርኔት ትስስርን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሏል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ አፍሪካን በዲጂታል የሚያስተሳስር የ"ኮኔክቲቪቲ ኮሪደር" ለመፍጠር የተወሰደ ወሳኝ ርምጃ ነው።
አክለውም ይህ ፕሮጀክት አፍሪካዊ አጋርነትን በተግባር የሚያሳይና ለአህጉሪቱ ኦፕሬተሮች የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እንደ አርዓያ የሚወሰድ ነው ብለዋል።
የጅቡቲ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አሶዌ ቡህ በበኩላቸው፤ ሆራይዘን በቀጠናው የቴሌኮም መሠረተ ልማት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና የዲጂታል ሉዓላዊነትን የሚያጠናክር ስትራቴጂካዊ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የሱዳቴል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማግዲ ኤም አብደላ ታሃ ፕሮጀክቱ በቴሌኮም ኦፕሬተሮች መካከል ያለውን ፉክክር በትብብር በመተካት ለደንበኞች፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለግዙፍ የዳታ ኩባንያዎች አዲስ እሴት እንደሚፈጥር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ ግዙፍ የፋይበር መስመር ዝርጋታ ኢኮኖሚን ከማጠናከር ባለፈ፣ ቀጣናውን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ ጠንካራ እና አስተማማኝ የኢንተርኔት መግቢያ (ጌት ዌይ) እንደሚያደርገው በስምምነቱ ወቅት ተመላክቷል።