የብሪክስ ስብስብ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሳየ ያለው ሳቢነት፣ የብዙ ሀገራትን ትኩረት ወደ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ እየሳበ ይገኛል።
እንደ ፕሮፌሰር አህመድ ኢብራሂም ትንታኔ፤ በርካታ የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት የኅብረቱን ደጃፍ በከፍተኛ ፍላጎት እያንኳኩ ያሉት፣ አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ሁሉንም በእኩልነት ማስተናገድ ባለመቻሉና ፍትሐዊ ውክልናን በመጠማታቸው ነው።
ይህ ፍላጎት አባል ሀገራቱ በሀገር ውስጥ በገንዘባቸው ግብይት እንዲፈጽሙ ከሚያበረታታው አቅጣጫ፣ ከራሳቸው የልማት ባንክ መጠናከርና ከስልታዊ የኢኮኖሚ ጥገኛነት ለመውጣት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት ይመነጫል።
ይሁን እንጂ ስብስቡ አዲስ የዓለም ሥርዓትን ለመቅረጽ በሚያደርገው ጉዞ እንደ የጋራ ራዕይ መሳለጥ፣ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶችና የተቋማዊ አወቃቀር ማሻሻያዎችን የመሰሉ ውስጣዊ ፈተናዎች ከፊቱ ተደቅነዋል።
ብሪክስ አዲሱን የዓለም ሥርዓትን በብቸኝነት ይቀርጻል ተብሎ ባይገመትም፣ አሁን ያለውን የአንድ ወገን የበላይነት ሚዛን በማስተካከል ረገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ወደፊት የሚመጣው ዓለም አቀፋዊ መስተጋብር በርካታ ኃይሎች የሚሳተፉበትና የተለያየ አማራጭ የሚቀርብበት “መልቲ-ፕሌክስ” (Multiplex) ዓለም እንደሚሆን ይጠበቃል።
የብሪክስ ስኬት የሚለካው ሌላ አምባገነናዊ የበላይነት በመፍጠር ሳይሆን፣ የትኛውም ኃይል በብቸኝነት ዓለምን እንዳይቆጣጠር በማድረግና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድምጽ በእኩልነት እንዲሰማ በማስቻል ላይ ነው።
ዓለም እየተለወጠች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ስብስቡ ፍትሐዊና ሁለገብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ለመገንባት እንደ ትልቅ አማራጭ ኃይል ሆኖ ይቀጥላል ይላሉ የቢዝነስ ቱዴይ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ዳቶ በማጠቃለያቸው።
በሰለሞን ገዳ