የዓድዋ ድል በመላው አፍሪካውያን ዘንድ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ፣ የፓን አፍሪካዊነት መንፈስን ያጠናከረና ዓለም ለአፍሪካ ያለውን አመለካከት የቀየረ ታላቅ ድል መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ሁለተኛውን የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በንግግር በከፈቱበት ወቅት ነው።
ኢንጂነር አይሻ በንግግራቸው፤ የዓድዋ ጦርነት ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን ለክብር፣ ለነፃነትና ለእኩልነት የቆመ የታሪክ አምድ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ ኢትዮጵያውያን በጋራ ትብብር ያረጋገጡትና ዓለም ለአፍሪካ ያለውን አመለካከት የቀየረ መሆኑንም አብራርተዋል።
አፍሪካውያን የጋራ የደኅንነት ስጋቶችንና የኢኮኖሚ ተጋላጭነቶችን ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
“መደጋገፍ ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ የዓድዋ መንፈስ አህጉራዊ ትብብርን እንድናጠናክርና የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልቶ እንዲሰማ ጥሪ ያቀርባል ብለዋል።
ጥሪውን አክብረው የተገኙ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች መገኘትም ለነፃነትና ለሉዓላዊነት ለሚሰጠው ዋጋ ትልቅ ምስክር መሆኑን ጠቁመዋል።
በላሉ ኢታላ
#EthiopianBroadcastingCorporation #Ethiopia #Adwa130 #AfricaDefenseMinisterConference #PanAfricanism