Search

የመሪዎች ውይይት የኢትዮጵያና አዘርባጃንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል - ቢልለኔ ስዩም

እሑድ የካቲት 22, 2018 98

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በአዘርባጃን ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ምዕራፍ ማሸጋገሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ኃላፊዋ ጉብኝቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያና አዘርባጃን መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል አቅም ከአዘርባጃን የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት በጋራ ኢንቨስትመንት ለማልማት ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።

በዚህም በንጹህ ኢነርጂ ልማት ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ዕድሎች መለየታቸውን አመልክተዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ በስፋት እየተገበረችው የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአዘርባጃን በኩል ትልቅ አድናቆት እንደተቸረው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ ከተሞቿን ለማዘመን እና ዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋፋት አዘርባጃን ትልቅ የልምድ ምንጭ መሆኗንም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያና በአዘርባጃን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በቢታኒያ ሲሳይ

#EBC #Ethiopia #Azerbaijan #Diplomacy #AbiyAhmed #BilateralRelations #cooperation