በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ወታደራዊ ግጭት አዲስ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ቅዳሜ ጠዋት በተሰነዘረ የሚሳኤል ጥቃት የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
በጥቃቱ ከ86 ዓመቱ መንፈሳዊ መሪ በተጨማሪ ሴት ልጃቸው፣ የልጃቸው ባል እና የልጅ ልጆቻቸው ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎ የኢራን መንግስት በአገሪቱ የ40 ቀናት ብሄራዊ ሃዘን አውጇል።
ከእ.ኤ.አ. 1989 ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩት አያቶላ አሊ ኻሚኒ፣ ከጥቃቱ ሳምንት በፊት ለእስራኤልና ለአሜሪካ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ ጥቃት በኢራን የስርዓት ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
ህልፈቱን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ፤ በባህሬን፣ በኳታር፣ በኩዌት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤል ጥቃቶችን ሰንዝራለች።
በተለይም በባህሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ያነጣጠረው ጥቃት መጠነ ሰፊ መሆኑ ተዘግቧል።
ይህ ወታደራዊ ውጥረት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ ጀምሯል። ኢራን 30 በመቶ የዓለም ንግድ የሚያልፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥን እንደምትዘጋ ያስታወቀች ሲሆን፣ በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎችም በቀይ ባህር በኩል መርከቦች እንዳያልፉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ ተከትሎ የቀጠናው አገራት የአየር ክልላቸውን ለበረራ ዝግ ያደረጉ ሲሆን፣ አገራቱም ወታደራዊ ዝግጁነታቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሳድገዋል።
#EBC #Iran #Israel #USA #AyatollahKhamenei #MiddleEastConflict #HormuzStrait #RedSea #GlobalEconomy