Search

በምክክር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር

ማክሰኞ የካቲት 24, 2018 46

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን ኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ መንግሥት እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ የሐሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት እንዲቻል የተቋቋመ ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል።

በኮሚሽኑ መቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 የኮሚሽኑ ዓላማ በግልፅ የተደነገገ ሲሆን በተለይም በአንቀፅ 6 (3) ላይ የሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትን አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ መከናወን እንዳለባቸው፤ ለዚህም ተፈፃሚነት ኮሚሽኑ የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተደንግጓል።

ይህንን መነሻ በማድረግ በሀገራዊ ምክክር ሂደትአዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠርማለት ምን ማለት እንደሆነ መመርመሩ በሂደቱ ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ሚና ለማጉላት በእጅጉ ወሳኝ ነው። አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የሚፈጠረው የምክክር ባለድርሻ አካላት በሂደቱ በሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራዊ ምክክር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር የሚችልባቸው መንገዶች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።

1.  የፖለቲካ ባህል ማሻሻያ

የሀገራዊ ምክክር ሂደት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን በሀገራቸው መፃኢ እድል ላይ እንዲነጋገሩ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሲሆን ንግግርን እና ውይይትን ማዕከል ያደረጉ የሐሳብ ልዩነት መፍቻ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ይህም የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ ፉክክከርን በማስወገድ መከባበርን እና መግባባትን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ባህል እንዲፈጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። 

2.  በእውነት ላይ የተመረኮዙ ግንኙነቶች

የፖለቲካ ሥርዓት ማሻሻያዎች በፖለቲካ ልሂቃን እና በባለድርሻ አካላት መልካም ግንኙነት ይጀመራሉ። የሀገራዊ ምክክር ሂደትም ባለድርሻ አካላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲመካከሩ ሁኔታዎችን ሲያመቻች ለመልካም ግንኙነቶች ቅድሚያ የሚሰጥበትን አግባብ በመፍጠር ላቅ ባለ ሰብዓዊ ግንኙነት ዘላቂና መተማመን የተፈጠረበት እንዲሁም የመግባባት እርሾ የሚጠነሰስበትን ዓውድ ይፈጥራል።

3.  በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ከዋኞችን በሙሉ ማሳተፍ

እንደሚታወቀው በተለያዮ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ክስተቶች የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃን እና ባለድርሻ አካላት ራሳቸውን ከፖለቲካው መድረክ ሲያቅቡ ይስተዋላል። ይህ ድርጊት በሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የተሟላ እንዳይሆን ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል። በመሆኑም የፖለቲካ ልሂቃን በሀገራዊ ምክክር ሂደት በንቃት መሳተፋቸው ጠቀሜታው ከፍ ያለና ለትውልድም በጎ አሻራ የሚጥል መሆኑን በመገንዘብ ሀገራቸውን እንዲያግዙ ኮሚሽኑ ይጠይቃል።

4.  የፖለቲካ ፋይዳ ለሀገር የሚኖረውን ጥቅም መረዳት

የሀገራዊ ምክክር ሂደት የታለመለትን የሀገራዊ መግባባት ዓውድ ከመፍጠር በዘለለ በአከራካሪ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ትርክቶች ላይ የጋራ መረዳት እንዲኖር ያደርጋል። የጋራ መረዳቶቹ የግድ የጋራ መግባባት ላይ ሊያደርሱ ባይችሉም የጋራ መንገድ (Common Grounds) ለመፈለግ በሚደረገው ጉዞ እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስ ሆነው ያገለግላሉ። ይህም የፖለቲካ ልሂቃን ባሏቸው ልዮነቶችና እና መግባባቶች ላይ የጠራ ምስል እንዲኖራቸው በማድረግ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ያግዛል።

ስለሆነም የፖለቲካ ፋይዳ ለሀገራዊ መግባባት የሚኖረውን የጎላ ጠቀሜታ ለመረዳት የፖለቲካ ልሂቃን አበክረው ሊሰሩ ይገባል። ሲጠቃለልም የሐሳብ ልዩነቶች ለሁለንተናዊ እድገት አስፈላጊዎች በመሆናቸው መግባባት ላይ ሊደረስ ይገባል እንጂ በምንም አስተሳሰብ በጠላትነት ለመተያየት መንስኤዎች መሆን አይገባቸውም።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

#Ethiopia #NationalDialogue #EBC #ebcdotstream