በድሬዳዋ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ጥቅም ላይ ውለዋል።
የከተማዋ ፖሊስም አገልግሎቱን በማዘመን ወንጀሎችን እና አደጋዎችን መቀነስ እንደቻለ አሳውቋል።
የድሬዳዋ ፖሊስ የተቀናጀ የእንግዶች መረጃ አስተዳደር ሶፍትዌርን ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን መተግበሪያው በድሬድዋ ከተማ የሚገኙ ማንኛውም የመኝታ አገልሎት የሚሰጡ ተቋማት የሚገለገሉበት መተግበሪያ መሆኑን ነው የተገለጸው።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክተር ኮማንደር መሃመድ አደም በኢቢሲ አዲስ ቀን ከራስ አንደበት መሰናዶ ላይ እንደገለጹት፤ በመተግበሪያው ከወንጀል ጋር በተያያዘ ለፖሊስ ጥቆማ ለመስጠት ይረዳል።
ሌላኛው ለፖሊስ የመረጃ ምንጭ በመሆን የሚያገለግለው 24 ሰዓት የወንጀል ሁነቶችን የሚከታተለው ማዕከል ነው ብለዋል።
ይህም በመንገድ ዳር ካሜራ እና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ እየተሰራበት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የጦር መሳሪያዎች መመዝገቢያ እና ማስተዳደሪያ ስርዓት የተሰኘ መተግበሪያ በማበልፀግ አገልግሎት ላይ ውሏል ብለዋል፡፡
“ታደግ” የተሰኘው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃዎችን የሚያስተዳድረው መተግበሪያ በሳምንቱ የደረሱ አጠቃላይ አደጋዎችን በመመዝገብ የትራፊክ ሥራን የሚያከናውን እና ስምሪትን የሚያሳልጥ መተግበሪያ መሆኑንም ነው ኮማንደር መሃመድ አደም የገለፁት፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream#Diredawa #application