Search

አይቻልምን ያሸነፈው የሕዳሴው ግድብ

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 39

ከኢትዮጵያ ወንዞቿ መካከል ግዙፉ ዓባይ የዘመናት ቁጭትነቱ አብቅቶ ለልማት እየዋለ ይገኛል።  

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከጅምሩ አንስቶ የአይቻልም መንፈስን የሰበረ እና የቀጣናው ሀገራትን በልማት ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።

ኑሯቸውን በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ፓስተር ሳሙኤል ጌታቸው (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "የግድቡ የመሰረተ ድንጋይ ሲጣል ለፍፃሜው ስለመድረሱ እርግጠኛ አልነበርኩም" ይላሉ፡፡

ፕሮጀክቱ አይሳካም የሚል ግምት እንደነበራቸውም አልሸሸጉም።

በቁርጠኛ አመራሮች ምክንያት ግን ለዛሬ ድል በቅተናል ይላሉ።

በዓባይ ግድብ ያልተባበረ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም የሚሉት ፓስተር ሳሙኤል ፤ ምንም እንኳን የመጠናቀቁ ጉዳይ ጥያቄ ቢፈጥርባቸውው ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን ማድረጋቸውን አይዘነጉትም።

በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊን ከሕጻን እስከ አዋቂ ለሕዳሴ ግድብ ያደረጉት አበርክቶ ላቅ ያለ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የሕዝብ ድጋፍ ያልተለየው የሕዳሴ ግድብ ዛሬ ላይ እውን ሆኗል፤ ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ሥራም ተከናውኗል ይላሉ።

በአፍሪካ ትልቁ ግድብ በመሆኑም ለኢትዮጵያዊያን ብሎም ለአፍሪካዊያን ትልቅ ኩራት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ግድቡ የአይቻልም መንፈስን ሰብሮ ፤ የይቻላል መንፈስን ያሰረፀ ብሔራዊ አርማ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያዊያን በሕብረት ብንሰራ ከስኬት እንደምንደርስ ያሳየ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ያነሳሉ።

የዳያስፖራው ማኀበረሰብም በግድቡ ግንባታ ያሳየውን አንድነት በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም ማጠናከር አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

 

በሜሮን ንብረት