Search

የሆርሙዝ ሰርጥ ወቅታዊ ሁኔታና የነዳጅ ዋጋ ግሽበት

ሰኞ መጋቢት 07, 2018 59

በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ፣ ስትራቴጂካዊው የሆርሙዝ ሰርጥ ለአሜሪካና ለወዳጆቿ ዝግ መሆኑን ቴህራን አስታውቃለች።

የዓለማችን አንድ አምስተኛ የነዳጅ ምርት በሚያልፍበት በዚህ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ላይ፣ ኢራን ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገች መሆኑንም ገልጻለች።

ባለፈው መጋቢት 2 ቀን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ዋና አዛዥ አማካሪ ኢብራሂም ጃባሪ፣ ሰርጡ "ዝግ" መሆኑንና ማንኛውም መርከብ ለመሻገር ቢሞክር በኢራን ባሕር ኃይል እርምጃ እንደሚወሰድበት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ይህም  በዓለም አቀፉ የነዳጅ ገበያና በትራንስፖርት መስመሮች ላይ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል። በተለይ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ዋና ምክንያት ሆኗል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በበኩላቸው፣ በርካታ ሀገራት መርከቦቻቸው በሰላም እንዲያልፉ ጥያቄ እያቀረቡላቸው መሆኑን ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የተወሰኑ የሀገራት መርከቦች እንዲያልፉ መፈቀዱን ቢጠቁሙም፣ የትኞቹ ሀገራት እንደሆኑ ግን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

ይሁን እንጂ የቻይና፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ቱርክዬ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ እንዲያልፉ ፈቃድ ማግኘታቸውን አልጀዚራ በዘገባው አመላክቷል።

አሁንም ግን የትኞቹ ሀገራት ከኢራን ጋር ድርድር እያደረጉ እንደሆነና የትኞቹ መርከቦች የሰላም መተላለፊያ ፈቃድ አገኙ የሚለው ዓለም አቀፍ ትኩረት ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ሰርጥን ለማስከፈት በሚደረገው ጥረት የአውሮፓ አጋሮችና የአረብ ሀገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን የዋይት ሃውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በተለይ የኔቶ አባል ሀገራት የባሕር መተላለፊያው ክፍት እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል።

#EBC #MiddleEastConflict #HormuzStrait #OilPrice #GlobalEconomy #EnergySecurity