በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ የደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈና መሪር ሐዘን ያስከተለ ቢሆንም፤ በዚህ መከራ ውስጥ የታየው የአቶ ዳመነ ደበበ ጽናት ግን ለብዙዎች ተስፋንና ብርታትን የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል።
መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም አደጋው በተከሰተበት ወቅት፣ አቶ ዳመነ ሌሎች ተጎጂዎችን ለማዳን በፍጥነት ወደ ስፍራው ቢያቀኑም፤ በዚያው ቅጽበት ግን ባለቤታቸውን፣ ልጃቸውን፣ የልጃቸውን ሚስትና የልጅ ልጃቸውን በአደጋው ማጣታቸውን ይገልጻሉ።
በደቂቃዎች ልዩነት አራት የቤተሰብ አባላትን በዓይናቸው እያዩ የማጣት ከባድ ፈተና የገጠማቸው እኚህ አባት፤ በአካባቢው በነበረው አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ምክንያትም የቤተሰቦቻቸውን አስክሬን ለማግኘት ለአራት ቀናት በመከራ ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል።
ይሁን እንጂ ይህ መሪር ሐዘን የአቶ ዳመነን ታላቅ ስብዕና ሊሰብረው አልቻለም። እንዲያውም ከራሳቸው ሐዘን በላይ ለተጎዳው ማኅበረሰባቸው መቆምን መርጠዋል።
የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዳመነ፣ ለሌሎች ተጎጂዎች የመጽናኛ ተምሳሌት በመሆን ሕዝቡ ከደረሰበት ድንጋጤ ወጥቶ ወደ መደበኛ የልማት ሥራው እንዲመለስ በትጋት እያስተማሩ ይገኛሉ።
የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳመነ፣ ለተጎጂዎች እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም አካባቢው ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በመሆኑ፣ መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ አማራጭ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመስገን ተስፋዬ
#ጋሞ #የመሬትመንሸራተት #EthiopianBroadcastingCorporation #GamoZone #LandslideEthiopia #HumanitarianAid