Search

በ2.9 ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባው የሻሸመኔ-ሃላባ መንገድ ግንባታ 42 በመቶ ደረሰ

ሰኞ መጋቢት 07, 2018 49

የፌደራል መንግሥት በ2.9 ቢሊዮን ብር በጀት እያስገነባው የሚገኘው የሻሸመኔ - ሃላባ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ከ42 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ከሞጆ - ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ጋር የሚያገናኘውና 68 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ፕሮጀክት፣ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል።
መንገዱ የምዕራብ አርሲ ዞንን ከሃላባ ዞን ጋር የሚያስተሳስር በመሆኑ፣ በቀጣናው ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የነጌሌ ቦረና ፕሮጀክቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የቡድን መሪ አቶ ደረጄ ቦጋለ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በግንባታው ሂደት ላይ እንቅፋት የነበሩ የወሰን ማስከበር ችግሮች በመቀረፋቸው፣ በአሁኑ ወቅት ስራው በተሻለ ፍጥነትና በትኩረት እየተከናወነ ነው።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከዋናው የሻሸመኔ - ሃላባ መስመር በተጨማሪ፣ በሁለቱ ከተሞች ውስጥ የሚከናወኑ ባለ ሁለት አቅጣጫ የአስፋልት መንገዶችንም የሚያካትት ነው።
ይህም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ አካባቢዎችን ከዋናው የፍጥነት መንገድ ጋር በማገናኘት፣ የንግድና የማህበራዊ ትስስርን ለማቀላጠፍ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።
በአሁኑ ወቅት የ16 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ስራ የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የጠረጋ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የአፈር ቆረጣና ሙሌት እንዲሁም የሰብቤዝ (Sub-base) እና የቤዝኮርስ (Base course) ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
በሚካኤል ገዙ