Search

የቁንድዶ ፈረሶች፤ "የጋማ ነዳጆች" እና የተራራው ግርማ ሞገስ

ሰኞ መጋቢት 07, 2018 58

በኤጀርሳ ጎሮ ሰማይ ስር፣ በኦሮሚያና በሶማሊ ክልል ድንበር ላይ አንዳች ተዓምር አለ። ቁንድዶ ተራራ። ጫፉ ላይ ውሃና አረንጓዴ ምንጣፍ የታደለ፣ ተፈጥሮ በቅናት የጠበቀችው ገነት። 
እዚያ ተራራ ጫፍ ላይ ስትቆሙ ግን ከአየር ንብረቱ በላይ የሚያስገርማችሁ ሌላ ‘የተራራ ወርቅ’ ታገኛላችሁ የቁንድዶ የዱር ፈረሶች። 
“ደግሞ ስለ ዱር ፈረስ ምን ያስጨንቃል?” ብላችሁ ካሰባችሁ፣ ተሳስታችኋል። እነዚህ ፈረሶች እንደመናኛ ፈረስ በየመንገዱ የምናያቸው አይደሉም። 


ይልቁንም አንጡራ የኢትዮጵያ ሀብት፣ እንደ ቀይ ቀበሮና እንደ ዋሊያ በዓለም ላይ በሌላ በየትም ስፍራ የማይገኙ ድንቆች ናቸው። ግርማ ሞገሳቸው ያስፈራል፤ ወደ እነሱ ለመጠጋት ትንፋሽን መግታት ይሻል። ግዙፍ ናቸው፤ ጋማቸው ከአንገታቸው ተንጠልጥሎ መሬት ሊነካ ይተናነቃል። ግልገሎቹ እንኳ ሳይቀሩ ንቁና ባለግርማ ናቸው። 
በዱር ለዘመናት ከነብርና ከጅብ ጋር እየታገሉ በመኖራቸው፣ አንዳች የሚሰነዝር ድምፅ ቢሰሙ ጆሯቸውን ቀስረው ጠላትን በደቦ የመከላከል ጥበባቸው ያስደምማል። ድንገት ጥርጣሬ ከገባባቸው ደግሞ እርስ በእርስ ተጠራርተው በአንድነት ይቆማሉ፤ የኅብረታቸው ውበት ከሰው ልጆች በላይ ያስተምራችኋል።


የዱር ፈረስ በአፍሪካ ምድር ናሚቢያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ ቢገመትም፣ የቁንድዶዎቹ ግን ዝርያቸውም ሆነ አመጣጣቸው እስከዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖ የቀጠለ ‘የተፈጥሮ ምሥጢር’ ነው። 
ባለሙያዎች እንደሚሉት እነዚህ ፈረሶች የማይነጥፍ የዘረ-መል (ጄኔቲክ) ሀብቶች ናቸው። በሽታን የመቋቋም ብቃታቸውና ጥንካሬያቸው ቢጠና፣ ለዓለም ሌላ ድንቅ ሀብት ሊሆኑ የሚችሉ የኢትዮጵያ “የጋማ ነዳጆች” ናቸው ይሏቸዋል።
ይህ አስደናቂ ተራራና በምሥጢር የተሞሉት ፈረሶች በሌላ ሀገር ቢሆኑ ኖሮ፣ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያስገኝ የቱሪስት ጎርፍ ይከሰትባቸው ነበር። 
ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በቁንድዶ ያደረጉት ጉብኝት፣ ይህንን የተዳፈነ ወርቅ እንደ ‘ገበታ ለሀገር’ ለዓለም ይፋ የሚያደርግ ይሆን?