Search

ለምርምር ወደሕዋ እንድትጓዝ የተመረጠችው ኢትዮጵያዊት

ረቡዕ ጳጉሜን 05, 2017 54

እመቤት መሀባው ትባላለች። ከልጅነቷ አንስቶ ለሕዋ ሳይንስ ፍቅር እንደነበራት ታስታውሳለች።
በኋላም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ በሕዋ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ስኮላርሺፕ አግኝታ ወደሕንድ አቀናች።
በኋላም አሜሪካ ውስጥ በሕዋ ሳይንስ ምርምር ላይ የሚሰራውን ታይታንስ ስፔስ ኢንዱስትሪን መቀላቀል ችላለች።
በዚያም በኤሮስፔስ ኢንጂነርነት ሙያዋ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነች ይገኛል።
የምትሰራበት የሕዋ ምርምር ተቋም በእ.አ.አ. በ2029 ወደጠፈር ለሚያደርገው ጉዞ እመቤት መሀባውን ከተጓዥ ተመራማሪዎች መካከል አንዷ እንድትሆን መርጧታል።
ለዚህ ምርጫ የተለያዩ መስፈርቶች ቢኖሩትም፤ ግዳጁን ለመፈፀም በአካል፣ በስነልቦናም ሆነ በምርምር ሥራዋ ብቁ መሆኗ ካስመረጧች ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ነው የገለፀችው።
ወጣቷ የሕዋ ሳይንስ ባለሙያ ለጠፈር ጉዞዋ የሚረዳትን የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገች ሲሆን፤ በቡድን የሚደረገውን ዝግጅት ደግሞ እ.አ.አ. በ2026 አካባቢ እንደምትጀምር ነው የተናገረችው።
በምድር ምህዋር ላይ በመሽከርከር የተለያዩ ምርምሮችን ማከናወንን የሚያካትተውን የሕዋ ጉዞ ዕድሉን የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ እንደምትጠቀምበት ተናግራለች።
በተለይም ወደሕዋ በሚኖራት ጉዞ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ይዛ የመሄድ ፍላጎት እንዳላትም አሳውቃለች።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ዕውቅና እያገኘች የመጣችው እመቤት፤ ለስፔስ ጄኔሬሽን አድቫይዞሪ ካውንስል የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን እያገለገለች ይገኛል።
ከአፍሪካ ስፔስ ሊደርስ አዋርድ በ2024 ከአፍሪካ 4 ተሸላሚ ወጣቶች መካከል አንዷም ነበረች።
ዓለም አቀፉ አስትሮናውቲካል ፌዴሬሽንም በ2025 ተስፈኛ ከሆኑ የሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች መካከል አንዷ መሆኗን አሳውቋል።
 
በጌትነት ተስፋማርያም