በሄናን ግዛት የባህል ቅርስ እና አርኪኦሎጂ ተቋም አርኪኦሎጂስቶች እንደገለፁት፣ ከ8,000 ዓመታት በፊት የነበሩ የቻይና ጥንታዊ የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች በጂያሁ ቁፋሮ ቦታ ተገኝተዋል። ይህ ግኝት ቀደምት የሬሳ ሳጥን እና ክፍል ያለው የቀብር ሥርዓት በቅድመ-ታሪክ ቻይና ውስጥ እንደነበረ የሚያሳይ ነው።
በውያንግ አውራጃ በርካታ የአጥንት ዋሽንቶች፣ የዔሊ ዛጎሎች፣ የሸክላ ዕቃዎች እና የድንጋይ መሣሪያዎች የተገኘ ሲሆን ይህም ስለ ቀደምት የቻይና ሥልጣኔ መረጃ ይሰጣል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዌይ ሺንግታኦ እንደተናገሩት፣ ይህ ግኝት የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች ከዚህ በፊት ከታሰበው ከ2,000 ዓመታት ቀደም ብሎ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ያመለክታል።
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በቁፋሮው ቦታ ከ200 በላይ መቃብሮችን ያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 10 ያህሉ የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች ማስረጃዎች እንዳሏቸው ተገልጿል።
አርኪኦሎጂስቶች እንዳሉት አንዳንድ ሳጥኖች 2 ሜትር ርዝመት፣ 0.6 ሜትር ስፋት እና 6 ሴንቲሜትር ውፍረት አላቸው።
የእነዚህ ግኝቶች መገኘት፣ የቀብር ሥርዓቶች ከበፊቱ ከታሰበው ከ2,000 ዓመታት ቀደም ብሎ መመሥረታቸውን ያመለክታል።
በሰለሞን ገዳ