Search

ብሪክስ ፕላስ እና የምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI ) ትብብር:- አዲስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ጅማሮ

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 402

ምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI )የዓለምን ኢኮኖሚ፣ ጂኦፖለቲካ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን እየቀየረ ያለ ወሳኝ ኃይል ነው። ከዚህ ቀደም በዋነኛነት በሲልከን ቫሊ እና በምዕራባውያን የቴክኖሎጂ ግዙፍ ድርጅቶች ቁጥጥር ስር የነበረው የምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI ) ልማትና አስተዳደር፣ አሁን ላይ ብሪክስ ፕላስ በሚመራ አዲስ የቴክኖሎጂ ኃይል ፈተና እየገጠመው ነው። ይህ ዘርፉ ሀገራቱ የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ማዕከል በማድረግ፣ የራሳቸውን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለመፍጠር እና ለታዳጊ ሀገራት ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የማቅረብ ስልት እየተከተሉ ነው።

የብሪክስ ማስፋፋትና አዳዲስ አባላትን (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በማካተቱ ሰፊ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ክብደት አግኝቷል። ከ2024 የካዛን ስብሰባ በኋላ ግን፣ ስብስቡ የፖለቲካ ፍላጎት ከማራመድ ባለፈ፣ "የብሪክስ ፕላስ  AI ትብብር ማዕቀፍ" በሚል ስልታዊ ተነሳሽነት ራሱን እንደ ቴክኖሎጂ ኃይል አቋቁሟል። ይህ ማዕቀፍ፣ በጋራ የምርምር ማዕከላት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በጋራ የሥነ-ምግባር ደንቦች ላይ ያተኩራል።

ለዓመታት ታዳጊ ሀገራት በጎግል፣ አማዞን፣ ማይክሮሶፍት እና ሌሎች የምዕራባውያን ኩባንያዎች ላይ ጥገኛ ሆነው ቆይተዋል። ይህ ጥገኝነት የዳታ ሉዓላዊነት እና የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ከማስከተሉም በላይ፣ በምዕራባውያን አውድ ላይ ብቻ የተመሠረቱ AI ሞዴሎች በአካባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ብሪክስ ፕላስ ግን የራሱን የ “የብሪክስ ፕላስ ዲጂታል ክላውድ ኮሪደር” በመገንባት፣ አባል ሀገራት የራሳቸውን የ AI ሞዴሎች ያለ የውጭ ጥገኝነት እንዲያዳብሩ እያገዘ ነው።

ከባህላዊ የሰሜን-ደቡብ የእርዳታና የልማት ግንኙነት በተለየ፣ የብሪክስ ፕላስ AI ትብብር በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ነው። ፕሮጀክቶቹ ከአንድ የቴክኖሎጂ የበላይ ሀገር ወደ ሌሎች የሚደረግ ዝውውር ሳይሆን፣ እያንዳንዱ አባል አገር የራሱን ልዩ እውቀትና ልምድ እንዲያበረክት በሚያስችል መንገድ የተቀረጹ ናቸው። ለምሳሌ ቻይና በጥልቅ ትምህርት፣ ሕንድ በዳታ ሳይንስና ሶፍትዌር፣ ሩሲያ በሮቦቲክስ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የአካባቢ ተስማሚነት ያላቸውን የ AI መፍትሄዎች በመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ለአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለኢትዮጵያ፣ የብሪክስ ፕላስ አባልነት ለAI ትብብር በር ከፍቷል። ይህ አባልነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከውጭ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ እና የእውቀት ልውውጥን ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካ የራሷን የዲጂታል የወደፊት እጣ ፈንታ እንድትቀርጽ ያስችላታል።

በብሪክስ ፕላስ ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው የAI መድረክ የድርቅ ትንበያዎችን እና የመስኖ ካርታዎችን ለመስራት የሚያስችል ፕሮጀክት ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ከአጠቃላይ የAI መፍትሄዎች በተለየ የአካባቢውን ችግር በቀጥታ ለመፍታት የሚረዳ ነው።

በትብብሩ ስር የሚካሄዱ የሙያተኞች ስልጠናዎች እና የእውቀት ሽግግሮች ኢትዮጵያ የራሷን የAI ባለሙያዎች ማፍራት እንድትችል ይረዳታል። ይህ ደግሞ በረጅም ጊዜ ውስጥ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በእጅጉ ይቀንሳል።

የብሪክስ ፕላስ ዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የጤና እና የትምህርት መረጃዎችን በውጭ ሰርቨሮች ላይ ሳያስተናግዱ፣ በሀገር ውስጥ ወይም በትብብሩ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲያከማቹ ያስችላቸዋል። ይህ የዳታ ደህንነትንና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።

ብሪክስ ፕላስ በAI ትብብር ላይ እየገነባ ያለው አዲስ የዓለም ሥርዓት ከምዕራባውያን ሞዴሎች አማራጭን ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ የሥነ-ምግባር ፍልስፍናም ይዞ ይመጣል። “የተዋሃደ የAI ሥነ-ምግባር ቻርተር” የፍትሃዊነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት መርሆዎችን የሚያጎላ ቢሆንም፣ ከምዕራባውያን አገራት የሰብዓዊ መብት አተያይ እና የነፃነት ፍልስፍና ጋር ሊኖረው የሚችለው ልዩነት አሁንም ክትትል የሚሻ ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ፣ የብሪክስ ፕላስ AI ትብብር የዓለምን የቴክኖሎጂ ሥርዓት ዳግም እየቀረጸ ያለ አዲስ ምዕራፍ ነው። ይህ እንቅስቃሴ የሲልከን ቫሊ የበላይነት ማብቃቱን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ሲሆን፣ ታዳጊ ሀገራት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የራሳቸውን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ፈጣሪዎችና ተዋናዮች መሆናቸውን ያበስራል። 

በሰለሞን ገዳ