Search

ጥቅም ላይ የዋለ የምግብ ዘይትን ለአውሮፕላን ነዳጅነት

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 44

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁለት መቶ ሀገራት በሚሳተፉበትና ከዛሬ ጀምሮ በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጃፓናውያን በጥቅም ላይ ያዋሉትን የምግብ ዘይት ይዘው እንዲመጡ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በዚህ ስፖርታዊ ዝግጅቶችን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ፕሮግራም የአትሌቲክስ ውድድሮቹን ለመመልከት ወደስታዲየሞቹ ከሚመጡት ነዋሪዎች የሚሰበሰቡት በጥቅም ላይ የዋሉ ዘይቶች ወደ አውሮፕላን ነዳጅ እንደሚቀየሩ ታውቋል።

ለተለያዩ ጥብሳ ጥብሶች ጥቅም ላይ ውሎ የሚተርፈው የምግብ ዘይት ዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ (Sustainable Aviation Fuel /SAF) ለማምራት እንደ ግብአት የሚጠቅም መሆኑ ነው የተገለጸው።

ይህ አገልግሎት ላይ ከዋለ የምግብ ዘይት የሚዘጋጀው “SAF” በተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንደ አውሮፕላን ነዳጅ ያገለግላል።

በቶኪዮ መዘጋጃ ቤት እና ከታዳሽ ምንጮች ለአውሮፕላን የሚሆኑ የነዳጅ ውጤቶችን (SAF) በሚያመርት ካምፓኒ የተዘጋጀው ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ነዋሪዎች እንደ አትክልት ዘይት፣ የወይራ ዘይት የካኖላና የአኩሪ አተር ዘይቶችን ከመድፋት ይልቅ ለዚህ ጠቃሚ ተግባር እንዲያውሉት ከስታዲየሞቹ ውጭ ከሰማንያ በላይ ዘይት መሰብሰቢያ ጣቢያዎች መከፈታቸው ተገልጿል።

የፕሮግራሙ አዘጋጆች እንዳስታወቁት ጥቅም ላይ የዋሉ የምግብ ዘይቶችን ለአውሮፕላን ነዳጅነት መጠቀም ከመደበኛ ነዳጅ 80 በመቶ የካርበን ልቀትን የሚቀንስ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዘይቶችን ከመድፋት ይልቅ መልሶ መጠቀም መቻል የአካባቢ ብክለትንም እንደሚያስወግድ ነው ያስታወቁት።

የምግብ ዘይቶችን ወደ አውሮፕላን ነዳጅነት በመቀየር ሂደት ከአንድ ሺህ ሊትር በጥቅም ላይ የዋለ ዘይት 6 - 8 መቶ ሊትር የሚደርስ የአውሮፕላን ነዳጅ መቀየር ይቻላል።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #tokyo2025 #fuel #SAF #cleanenergy