Search

አልባኒያ ሙስናን ለመዋጋት የምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሚኒስትር ሾመች

እሑድ መስከረም 04, 2018 50

አልባኒያ፣ ሙስናን ለመዋጋት በማሰብ የማይደለል የዲጂታል ባለስልጣን ለመጠቀም ወስናለች።

ዲዬላ (Diella) የተሰኘውና ቀደም ሲል በመንግስት ድረ-ገጽ ላይ የነበረው የኤአይ ረዳት፣ ከዚህ በኋላ የመንግስት ግዥዎችን እንደሚመራ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢዲ ራማ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ“ዲዬላ በአካል የሚገኝ ሳይሆን በኤአይ የተፈጠረ የመጀመሪያው የሚኒስትሮች ካቢኔ አባል ነው።” ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም አልባኒያ የመንግስት ጨረታዎች ከሙስና 100% ነጻ እንዲሆኑ ለማድረግ አቅዳለች።

አልባኒያ፣ ባለፈው ዓመት ከ180 አገሮች ውስጥ በዓለም አቀፉ የሙስና አመለካከቶች መረጃ ጠቋሚ (Transparency International’s Corruption Perceptions Index) ላይ 80ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ነበር።

በአልባኒያ ባለፉት ወራትም በቆሻሻ አያያዝ ዙሪያ በተፈጠረ የሙስና ቅሌት ሰባት የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት የስልጣን አላግባብ መጠቀም ወንጀል ተከሰው ተፈርዶባቸዋል።

ይህ እርምጃ በአልባኒያ የመንግስት ኮንትራቶች አሰጣጥ ዙሪያ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የሙስና ችግር ለመቅረፍ እና የሀገሪቱን ወደ አውሮፓ ህብረት ለመግባት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ያለመ መሆኑን አርቲ ዘግቧል።

በሰለሞን ገዳ