Search

ሕዳሴ ሀገራዊ ጉዳይን በማስቀደም ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የታየበት ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ማክሰኞ መስከረም 06, 2018 7

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራዊ የጋራ ጉዳይን እንዴት ማስቀደም እንደሚቻል የታየበት ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
በኢቢሲ አዲስ ቀን 'የሀገር ጉዳይ' መሰናዶ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እጅግ ውስብስብ በሆኑ ዓመታት ውስጥ በዓባይ ጉዳይ ዘብ በመቆም ታሪክ ሰርተዋል ብለዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያዊ በቦንድ ግዢ እና በተለያዩ መንገዶች የፕሮጀክቱ ባለቤት መሆናቸውን አሳይተዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን አይችሉም የሚል ቅስቀሳ እንደነበር ገልጸው፤ ይሁንና ዜጎች ግድቡን እውን ለማድረግ በዓይነቱ ልዩ እና አኩሪ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ፈጥረው እንደነበር አምባሳደሩ አስታውሰው፤ በኢትዮጵያዊያን እና በመንግሥት ጥረት የዲፕሎማሲ ሥራው ላይ ድል መገኘቱን አንስተዋል።
ስለ አፍሪካ የነበረውን የተሳሳተ እሳቤ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀልብሰነዋል ብለዋል፡፡
ግድቡን ለመገንባት የተሄደበት መንገድ ለሌሎች ፕሮጀክቶች እንደ መንደርደሪያ ሊወሰድ ይገባል ሲሉም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት