Search

የአንጀት ካንሰር ሕመም በወጣቶች እና ጎልማሶች ላይ የመከሰት ዕድሉ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ማክሰኞ መጋቢት 08, 2018 42

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች በአንጀት ካንሰር እንደሚያዙ እና ሕመሙ በወጣቶች እና በጎልማሶች ላይ የመከሰት ዕድሉ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።

የአንጀት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ የሆነውን መጋቢት ወርን ምክንያት በማድረግ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ እንደተገለጸው፣ የአንጀት ካንሰር በሀገራችን በወንዶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘ ሲሆን፣ በጥቅል ደረጃ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ ሕመሙ ቀደም ሲል ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ይስተዋል የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን በወጣቶች ዘንድ በስፋት እየታየ ይገኛል።

ለዚህም ዋነኛ መንሥኤ ተብለው የተጠቀሱት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ እና ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ አልኮል መጠጣት እና ሲጋራ ማጨስ፣ ረጅም ጊዜ የቆየ የአንጀት ቁስል እና የዕድሜ መግፋት ናቸው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በካንሰር መከላከል ላይ ከፍተኛ ንቅናቄ መደረጉን የገለጹት ዶክተር ሕይወት፤ ኅብረተሰቡ የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በተጨማሪም አትክልት እና ፍራፍሬን ማዘውተር፣ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ሥጋዎችን ከመመገብ መቆጠብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሽታውን ለመከላከል ወሳኝ መንገዶች መሆናቸው ተመልክቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዚህ ሕመም የሚያዙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

በኤልሻዳይ ወንድማገኝ

#Ethiopia #EBC #worldcancermonth #worldcancersupport