ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሐሳብ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሰላም፣ በልማት እና በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣ አንድነት እንዲጠነክር፣ ትውልድ እንዲማር፣ በስነምግባር እንዲታነፅ፣ ታሪክን እና ቅርስን በመጠበቅ እንዲሁም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባት እና የሥራ ባህልን በማበረታታት ረገድ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት።
በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተቋማቱ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ ጉልህ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ለሕዝቦች ትሥሥር መጎልበት፣ በማኅበራዊ ልማት እና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎ፣ የሥራ ባሕልን በማስረጽ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ የበጎነት ሥራ መሥራት እንዲለመድ በማድረግ፣ ለመልካም አስተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት እንዲሁም ሰላምን በማስፈን እና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም ጠቃሚ ውይይት ማድራቸውን ገልጸዋል።
በውይይታችን የተነሡ በሥራ ሂደት ያጋጠሙ አንዳንድ ክፍተቶችን እና እንግልቶችን በቀጣይ በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክም ነበር።
ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትን እና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የወንጌላውያን፣ የካቶሊክ እና የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪዎች ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ እና ለሰጡት ገንቢ ሐሳብ በራሳቸው እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመግነዋል።