የማዕድን ሚኒስቴር በቅርቡ የ4.2 ቢሊየን ዶላር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርሟል። ይህ ስምምነት ሀገራችን ወደ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ እና ዘመናዊ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር የሚያሳልጥ ነው።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙም መሰረት መያዙን አብሳሪ ነው። በብረት፣ በፖታሽ እና በወርቅ ማዕድናት ላይ ያተኮረው ይህ ስምምነት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ሞተር ተደርጎም ይወሰዳል።
የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የውጭ ምንዛሬ
ይህ ፕሮጀክት የማዕድን ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት (GDP) የሚያበረክተውን ድርሻ ከ1 በመቶ ወደ 14 በመቶ ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ ያፋጥናል። ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ፣ ኢትዮጵያ ለብረት እና ሌሎች ምርቶች የምታወጣውን ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያስችላታል።
የብረት ማዕድን ለኢንዱስትሪ ግንባታ
ዜድ ዋይ ቲ ቢ-ዲ አይ ኤም (ZYTB-DIM) የተባለው ኩባንያ በየሁለት ዓመቱ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብረት ለማምረት ተፈራርሟል። ይህም ኢትዮጵያን በአሥር ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ ቀዳሚ የብረት አምራች ያደርጋታል።
የብረት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የግንባታ ወጪን ከመቀነሱም በላይ፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያለ ግብዓት እጥረት እንዲከናወኑ ይረዳል።
የፖታሽ ልማት እና የግብርና ምርታማነት
በአፋር ክልል የሚገኘው ከ11 እስከ 12 ቢሊዮን ቶን የሚገመተው የፖታሽ ክምችት በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ ሀብቶች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይህንን ሀብት ለማልማት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል። ይህም ለሀገር ውስጥ ማዳበሪያ ፍላጎት ዋስትና ከመስጠቱም በላይ፣ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች
እንደ አውስትራሊያ እና ብራዚል ያሉ ሀገራት የማዕድን ሀብታቸውን ለኢኮኖሚ ሽግግር ተጠቅመውበታል። አውስትራሊያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂን (Mining 4.0) በመጠቀም የማምረቻ ወጪዋን በ50 በመቶ ቀንሳለች። ብራዚል ደግሞ ማዕድኗን በጥሬው ከመላክ ይልቅ በሀገር ውስጥ እሴት በመጨመር የኢንዱስትሪ መሠረቷን አጠናክራለች። ኢትዮጵያም እንደ ብራዚል "ከጉድጓድ ወደ ፋብሪካ" የሚለውን መርሕ በመከተል ማዕድኗን እሴት ጨምራ ለገበያ ለማቅረብ መወሰኗ ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ ወሳኝ ነው። እንደ አውስትራሊያም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወጪ ቆጥባ ከራሷ ፍጆታ አልፋ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ብልፅግናዋን እውን ታደርጋለች።
ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ በማዕድን ዘርፉ 14 ሚሊዮን አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዷል። ይህም በወጣቶች የሥራ አጥነት ቅነሳ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ማዕድናቱ በሚወጡባቸው አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የውኃ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ በማድረግ ቀጣናዊ ትሥሥርን ያጠናክራል።
በአጠቃላይ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጫናዋን የምታቀልልበት፣ የኢንዱስትሪ መዋቅሯን የምታዘምንበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት የምታረጋግጥበት አዲስ ምዕራፍ ነው።
በለሚ ታደሰ