ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የጀመረችውን ሀገርን ከውጭ ጥገኝነት የማላቀቅ ስትራቴጂካዊ ጉዞ አጠናክራ ቀጥላለች።
ከእነዚህም መካከል የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የማሸጋገር (Transport Electrification) መርሐ-ግብር በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ስኬት መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገልጿል።
በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ የዓለም የነዳጅ ገበያ ከፍተኛ መናወጥ ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት፣ መንግሥት ከአራት ዓመታት በፊት የቀረጸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ ሀገርን ከፈተና የሚታደግ አርቆ አሳቢ ውሳኔ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።
ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋም እና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሚከተሉት አራት ዋና ዋና ነጥቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል፦
የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኃይል አጠቃቀም
የኤሌክትሪክ መኪናዎችን የመጠቀም ልምድን እንደ ሀገራዊ ባህል ማዳበር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ (Plug-in Hybrid) ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ ተጠይቋል።
በነዳጅ የሚሠሩትን ወደ ኤሌክትሪክ እና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ፣ ከዚያ በላይ የሆኑት ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እንዲቀየሩ ከመንግሥት እና ከግል ዘርፉ ጋር በቅንጅት ይሠራል ብሏል።
የመንግሥት እና የሕዝብ ትራንስፖርት ሚና
በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ያሉ ሁሉም የመንግሥት እና የፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ እንዲዘወሩ የተጀመረው ዕቅድ ወደ ሙሉ ትግበራ ይሸጋገራል።
በተጨማሪም ባቡሮች እና ባሶችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በወጣላቸው ታሪፍ እና መርሐ-ግብር ያለ መቆራረጥ እንዲሰጡ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል።
የአጠቃቀም እና የአነዳድ ባህል ለውጥ
ከአንድ ቤት ውስጥ ብዙ መኪናዎችን ይዞ መንገድ ከመውጣት ይልቅ፤ ተሽከርካሪዎችን በጋራ የመጠቀም ልምድ እንዲዳብር ጥሪ ቀርቧል።
በከተማ ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር ጉዞዎችን በእግርና በብስክሌት በማድረግ "አረንጓዴ ጉዞዎችን" ማሳደግ እንዲሁም ነዳጅን እና የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ የ"Eco-driving" የአነዳድ ስልጠናዎችን ለአሽከርካሪዎች መስጠት የሽግግሩ አካል ነው።
የጥራት ቁጥጥር እና የአካባቢ ጥበቃ
ተሽከርካሪዎች ወቅታዊ ጥገና እንዲደረግላቸው እና ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የጭስ ልኬት መመሪያን 100% በመተግበር ሁሉም ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ስታንዳርድ የጸደቁ የነዳጅ እና ጭስ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።
ይህ ሀገራዊ ጥሪ የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ለማዳን፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ እና ዜጎች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እንዳይጎዱ ለማድረግ የታለመ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገልጿል።
#Ethiopia #transport #oilprice #solutions