ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ስማርት ዲጂታል የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በዚህ ስምምነት ሁለቱ ተቋማት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒቶች እና የሕክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሶሉሽን በጋራ በመንደፍ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል ተብሏል፡፡
ዲጅታል ሶሉሽኑ አንድ ወጥ አሰራርና ቁጥጥር እንዲሁም በሰው ስራሽ አስተውሎት የሚደገፍ የደህንነት ጥበቃና መሰል ጉዳዮችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም በመረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔን በመስጠት የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አሰራርን በማቀላጠፍና ዘመናዊ አሰራርን በመተግበር የስራ ጫናን ለመቀነስ፣ የመድኃኒት ቁጥጥርን ለማሻሻልና የሕግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል።
የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ታማኝነትንና ግልፀኝነትን ለማስፈን የዲጅታል ሶልሽኑ መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ታማኝና ቀልጣፋ የግዥና አቅርቦት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት አግልግሎት ከሰው እጅ ንክኪ መራቅን የሚፈልግ በመሆኑ፣ ስምምነቱ ዲጅታል አገልግሎትን በዘርፉ በመዘርጋት ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ገልፀዋል።
በአገርነሽ አየልኝ