የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ነፀብራቅ የሆነው ሳይንስ ሙዚየም ዐዳጊዎች ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስም ሆነ በአጠቃላይ ስለ ሳይንስ ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እንዲል ከሚያስችሉ ማዕከላት መካከል አንዱ ነው፡፡
በሳይንስ ሙዚየሙ ቋሚ የሆነ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ በበርካቶችም እየተጎበኘ ይገኛል፡፡
ወደቋሚ ኤግዚቢሽኑ ቢመጡ ምን መጎብኘት ይችላሉ? ሲል የኢቢሲ ቅዳሜ መልክ መሰናዶ አስቃኝቶናል።
በቋሚ የኤግዚቢሽኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የሮቦት ቴክኖሎጂ እንዲሁም የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ አስመልክቶ ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባው የሚያመላክቱ ቴክኖሎጂዎች ይገኛሉ።
በኤግዚቢሽኑ የውኃ እና ኢነርጂ ክፍል ደግሞ ታዳሽ ኃይልን ተጠቅሞ ኢነርጂ የሚመነጭበትን መንገድ የሚያሳዩ ሞዴሎች አሉ።

ከእነዚህም ሞዴሎች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የሚያሳየው ሞዴል ሲሆን፤ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ሞዴልም በስፍራው ይገኛል፡፡
የግብርና እና ዘመናዊ የከተማ ልማትን የሚያሳዩ ክፍሎችም ተደራጅተዋል።
ኤሮ ስፔስ የተሰኘው የኤግዚቢሽኑ ክፍል ደግሞ የዓለም አቀፍ ሕዋ ጣቢያዎችን ሞዴል አካትቶ ይዟል፡፡
በተጨማሪም ቦይንግ 787 አውሮፕላን ምስለ በረራን በተግባር የሚለማመዱበት መሳሪያም ተገጥሟል። በዚህ ምስለ በረራ አማካኝነት በርካታ ሰዎች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን መቃኘትም ይችላሉ።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ