Search

ተሽከርካሪን ለመቆጣጠር ተመራጭ የሆነው የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂ

እሑድ መስከረም 11, 2018 67

በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ተቋማት እና ግለሰቦች የተሽከርካሪ እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር የሚረዳ ጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ላይ ናቸው።
የተሽከርካሪያቸውን ፍጥነት፣ ያለበት ቦታ እና የቆመበትን ሰዓት ጭምር በኮምፒውተራቸው የሚቆጣጠሩ ተቋማትም ከጊዜ ወደጊዜ ተበራክተዋል።
የተሽከርካሪ ጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂ ገጠማ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሳሙኤል ደጀኔ፤ በተለያዩ ከተሞች ላይ ተሽከርካሪዎች ተሰረቁ ሲባል ይሰማል ይላሉ።
ለዚህ መፍትሄ ለማበጀት ደግሞ የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ።
 
 
ቴክኖሎጂውን በማስገጠም የተሽከርካሪያቸውን አድራሻ በቀላሉ በስልካቸው አሊያም በኮምፒውተራቸው አማካኝነት መቆጣጠር የቻሉ፤ ንብረታቸው ቢሰረቅ እንኳን በፍጥነት ለማግኘት እንደማይቸገሩ ይገልጻሉ።
በሀገራችን የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ እምብዛም በመሆኑ የመኪና ስርቆት ሲከሰት የሚገኘው በአሰሳ ነው፤ ይህንን ስጋት ለመቀነስ ቴክኖሎጂውን አውቆ መጠቀም ይገባል ይላሉ።
ለተሽከርካሪዎች የጂ.ፒ.ኤስ ቴክኖሎጂ ገጠማ ከጀመሩ 4 ዓመታትን ማስቆጠራቸውን የገለጹት አቶ ሳሙኤል፤ አሁን ላይ ከአዲስ አበባ አልፎ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ ያዋሉ በርካታ ግለሰቦች እና ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ሀገራችን ወደ ዲጂታል እና ዘመናዊነት እየተሸጋገረች በመሆኑ፤ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ጭምር የሚሰሩ የጂ.ፒ.ኤስ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም ያስረዳሉ።
 
በመሀመድ ፊጣሞ