መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመደመር እሳቤ እየተመራ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ ገለፁ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜ እና ገንዘብን ከመቆጠብ ባሻገር ተጠያቂነትን በማስፈን ህዝብ የሚገባውን ክብር እና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ስለመሆኑ ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
በዲጂታል አገልግሎት የታገዘው ማዕከሉ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ስህተቶች የቱ ጋር እንደተፈጠሩ የሚያሳይ እና ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዳ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገር ዲጂታል አገልግሎቱ የሚያመነጫቸው መረጃዎች ለፖሊሲ ቀረፃ እና ቅልጥፍና ያለው አሰራር ለማስፈን ያገለግላል ብለዋል።
ለመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተሰጠው ትኩረት ቃልን የመጠበቅ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የመንግስትን ትልቅ እሳቤ እና ከትንሽ ጀምሮ ስራዎችን የማጠናቀቅ መርህ የምንመራበት ፍልስፍና ነው ሲሉ ገልፀዋል።
አገልግሎቱ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን ቀጣይ እስከ ቀበሌ ድረስ ለመስፋፋት ታስቧል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በሴራን ታደሰ
#EBC #EBCDOTSTREAM #Ethiopia #MESOB