Search

የተፈጥሮ ጋዝ ምንድን ነው?

ቅዳሜ መስከረም 24, 2018 120

ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር አስመርቃለች።
በተመሳሳይም በዓመት 1.33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ፕሮጀክትም አስጀምራለች።
ለመሆኑ ይህ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ከሌሎች ነዳጆች በምን ይለያል?
የተፈጥሮ ጋዙ በዋናነት ሚቴን (Methane) ከተባለ የጋዝ አይነት የሚሰራ ሲሆን፤ በጣም ዝቅተኛ በሆነ የሙቀት መጠን ማቀዝቀዝን በሚያካትት ሂደት ወደ ፈሳሽነት እንደሚለወጥም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የተፈጥሮ ጋዙ ከጥልቅ ጉድጓድ በሚወጣበት ጊዜ እንደ ነዳጅነት ከማገልገሉ በፊት እንዲጣራ ይደረጋል ይላሉ ባለሙያዎች።
ኢትዮጵያ ማምረት የጀመረችው የተፈጥሮ ጋዝ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለትራንስፖርት እንዲሁም ለቤት ፍጆታ የኃይል አቅርቦት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያና አማካሪ አዶናይ አብረሃ ናቸው፡፡
በአንድ ኪሎ ግራም የታመቀ (ኮምፕሬስድ የሆነ) የተፈጥሮ ጋዝ ለአንድ ተሽከርካሪ በአማካይ 34 ኪሎ ሜትር የሚያስጉዝ ሃይልን ይሰጣል ይላሉ።
ከዋጋው አንፃር ሲታይ ደግሞ ከአንድ ሊትር ቤንዚን ወይም ናፍጣ እጅግ ባነሳ ዋጋ በገበያው ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሰሩ መኪናዎችን ወደ ጋዝ በመቀየር የተፈጠረውን ዕድል መጠቀም ይገባል ያሉት ባለሙያው፤ ይህም ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ያስመረቀችው ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የአካባቢን ብክለትን ከመቀነስ አንፃር ከቤንዚን እና ከናፍጣ መሰል ነዳጆች የተሻለ ውጤታማ መሆኑንም የጠቆሙት።
በሀገረ ሕንድ ከ6ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች የተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።
የተፈጥሮ ጋዝ በኢትዮጵያ ያለውን የበካይ ጋዝ መጠን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት አዶናይ ቻይና፣ ብራዚል እና ህንድ የመሳሳሉ ሀገራት በስፋት ይጠቀሙበታል ብለዋል።
በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት አቅም ያለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ግንባታ ኢትዮጵያ የሚትከተለውን የአረንጎዴ ኢኮኖሚ ልማት በመደገፍ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በመሀመድ ፊጣሞ