ኢቲቪ ፓርላማ ቻናል የምክር ቤቶችን ተግባራት በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች፣ በተሟላ መንገድ ለኅብረተሰቡ እንዲደርሱ ያስችላል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፈቲያ አደን ገልጸዋል፡፡
አፈ ጉባዔዋ፤ ከዚህ ቀደም የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛና አስቸኳይ ጉባዔዎችን በተመለከተ ከሚቀርቡ አጭር መረጃዎች ውጪ፣ የምክር ቤቶቹን የተሟላ ተግባርና ኃላፊነት ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ በበቂ ደረጃ ሽፋን ያገኙ እንዳልነበር አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የኢቲቪ ፓርላማ ቻናል መከፈት፣ በሀገሪቱ ከፍተኛው የስልጣን እርከን ላይ የሚገኘውን የምክር ቤት ተግባርና ኃላፊነት በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች በተሟላ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።
ምክር ቤቶች ሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሕጎች ከማውጣት በተጨማሪ ተፈፃሚነታቸውን እንደሚከታተል ያነሱት አፈ ጉባዔዋ፤ የሕግ አወጣጥ ሂደትን ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ቻናሉ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
በተጨማሪም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎችን ለማጠናከርና ከወካይ ህዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች እና ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ መረጃን በማቀበል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በተለይ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት።
በቴዎድሮስ ታደሰ