ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች ከለላ መሆን የቻሉ የዘመናችን ኢትዮጵያዊት ዐርበኛ ናቸው። ለወገናቸው መከታ፣ ለሀገራቸው የክብር ምሰሶ፣ ለታሪካቸው ደግሞ የጽናት ተምሳሌት መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች አስመስክረዋል።
“ጀግንነት በየፈርጁ ነው” እንደሚባለው፤ ትላንት እነ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በዓድዋ አውድማ ላይ የጠላትን ወረራ በብልኃት እና በጀግንነት እንደመከቱት ሁሉ፣ ዛሬም እርሳቸው በሰብዓዊነት መስክ ታሪክን እየደገሙ ይገኛሉ።
የዘመናችን ጀግና ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር በሴቶች አካል እና ሥነ-ልቦና ላይ የሚሰነዘረውን የጥቃት ወረራ እየመከቱ ያሉ ዐርበኛ ናቸው።
"ለጎጂ ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ ጥቃቶች አልገዛም!" በማለትም ለሴቶች ነጻነት እና ክብር ግንባር ቀደም ሆነው ተሰልፈዋል።
ባለፉት ዓመታት ፍርሃትን እና ዝምታን በመስበር፣ ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች መጠለያ፣ የሕክምና ድጋፍ እና የሙያ ሥልጠና በመስጠት አዲስ ተስፋን አስጨብጠዋል።
"አንዲት ሴት በገዛ አካሏ እና ሞራሏ ላይ ሙሉ ሥልጣን አላት" የሚለውን መርህ አንግበው፣ ከተገፉት ጎን በመቆም የፍትሕ መዝገብ በመክፈት በነጻ የጥብቅና አገልግሎት ሰጥተዋል።
የወይዘሮ ማሪያን ዓላማ ደግፈው የተገፊዎችን ቁስል የሚያክሙ እና የወደቁትን ለማቅናት እንዲሁም በነጻ ጥብቅና የሚቆሙ የሕግ ባለሙያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም "እኛም ለሴቶች ክብር ዘብ እንቆማለን!" በማለት ተነስተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ