የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ "የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ" በሚል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው የዳኝነትና የዲሞክራሲ ተቋማት ያከናወኗቸውን ዓበይት ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል።
አፈ-ጉባኤው በንግግራቸው ተቋማቱ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቁ ሆነው እንዲደራጁ እንዲሁም ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ገልጸዋል።
ለእነዚህ ተቋማት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ የአመራርና የሰው ኃይል ብቃትን ከተሰጣቸው ኃላፊነት ጋር በተገናዘበ መልኩ የማሳደግ ሥራ መከናወኑን አቶ ታገሰ ጫፎ አስረድተዋል።
በተለይም ተቋማቱን ዘመኑን በዋጀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማስታጠቅና ማዘመን ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፣ የተጀመሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ዛሬ የሚገነቡት መሠረት ለነገው ትውልድ እንዲተርፍ ታስቦ መሥራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አፈ-ጉባኤው፤ ምክር ቤቱም የጀመረውን ሕገ-መንግሥታዊ የድጋፍና የክትትል ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።