ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለአፍሪካ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ እንዲሁም ለጥቁር ህዝቦች እኩልነት መሰረት የጣለው 130ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ለመታደም አዲስ አበባ ከተገኙት የአፍሪካ ወታደራዊ አመራሮች መካከል አንዷ የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ካቢኔ ሶይፓን ቱያ ናቸው።
ሚኒስትሯ በቆይታቸው የታዘቧቸው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እና የምግብ ዋስትና ሥራዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች እኩልነት መሰረት የጣለ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ የአሁኑ ትውልድም ከዚህ ታሪክ የአንድነትን ትምህርት ሊቀስም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች አፍሪካውያን በምቾት እንዲቀመጡ የሚያደርጉ አለመሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ "ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር አንዲት ሀገር ብቻዋን ልትጓዝ የምትችለው እስከ አንድ ወሰን ድረስ ብቻ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎች የሁለትዮሽ ተቋማት አማካኝነት የጋራ መንፈስን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዓለም በጠባብ ብሔርተኝነት እየተናወጠች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ አፍሪካውያን በራሳቸው ክበብ ብቻ ተወስነው የሚቀሩበት ጊዜ ማብቃት እንዳለበትና ይልቁንም አህጉሪቱን ወደ አንድ በሚያመጡ የጋራ እሴቶች ላይ ቆሞ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በላሉ ኢታላ