የኢቲቪ ፓርላማ ቻናል ስርጭት መጀመሩ በምክር ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራት በፍጥነት እና በጥራት ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፣ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ግልፅነትን ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገልጸዋል፡፡
ሚዲያ የአንድ ሀገር ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማፋጠኛ ነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ፤ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የምናመጣበት ሕዝብና መንግስትን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ የኢቲቪ ፓርላማ ቻናል ከምክር ቤት የሚወጡ ሕጎች፣ የሚከናወኑ የሕዝብ ውክልና ተግባራት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሂደቶች፣ ግብረመልሶች እና ውጤቶቻቸው ወደ ወከለን ሕዝብ ተደራሽ የሚደረግበት መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
አፈ ጉባዔዋ የመንግሥት ከፍተኛው የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛው ተቋም የሆነውን ምክር ቤት መረጃ ማድረስ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢቲቪ ፓርላማ ቻናል በመጀመሩየተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በሲሳይ ደበበ