ኢቲቪ ፓርላማ ቻናል በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ጀምሯል። የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢኒያም ኤሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የወል እውነቶቿ የበዙላት እና ገዢ ትርክት የፀናባት ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመሆን ኢቲቪ ፓርላማን ሥራ ጀምሯል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው፥ ኢቲቪ ፓርላማ ምክር ቤቱ የሕዝብ አስተያየቶችን በቀጥታ እንዲሰበስብ እና ውይይቶችን እንዲያካሂድ ቁልፍ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት።
ሕዝቡም የወከላቸው እንደራሴዎች እየሰሩ ያሉትን ሥራ የሚያውቅበት እና የሚሰሩ ሥራዎች ምን አይነት ሂደቶችን አልፈው ተግባራዊ እንደሚሆኑ የሚመለከትበት መሆኑን አንስተዋል።
የህፃናት ፓርላማም እንደ አንድ ይዘት አድርጎ በውስጡ የሚይዘው ኢቲቪ ፓርማ ፤ ለትውልድ ትብብርን የሚያስተምር እና የሕግ የበላይነትን እያፀና የሚሄድ ቻናል ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ ጥቂት ሀገራት ብቻ የራሳቸው የፓርላማ ቻናል እንዳላቸው ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፥ ኢትዮጵያም ይህን ማድረግ በመቻሏ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።