ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በ6ኛው የሁለቱ ምክር ቤቶ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የ2018 የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን በዝርዝር አስቀምጠዋል። እነዚህም፦
አንደኛ፥ ከሥርዓት መለዋወጥ ጋር የማይናዱ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ሕዝባዊ ብሔራዊ ተቋማት ለመፍጠር መንግሥት ፅኑ መሠረት በመጣል ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመትም አንድነታችንን እና ሰላማችንን በማይናወጥ ደረጃ ላይ ለማድረስ መንግሥት በተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ብሔራዊ የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋሞቻችን የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ እና የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብርቱ ተቋማት እንዲሆኑ መንግሥት በቁርጠኝነት ይተጋል ብለዋል።
ሁለተኛ፥ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማረቅ እና ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም፣ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግሥት ፅኑ እምነት አለው።
በዚህ እምነቱ የእርቅ እና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።
ምንም እንኳን በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግሥት ሙሉ ዝግጁነት እና ዘመናዊ አቅም ቢኖረውም፤ የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂም እና ቁርሾ አናወርስም የሚል መርህ በመከተል በዛሬ ብልሃት እና ትዕግሥት ለነገ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መርጧል።
ይህ እምነት ሀገራዊ መግባባትን ለመትከል፣ ዘላቂ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥትን ለመመሥረት ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሆነም ነው ፕሬዚዳንት ታየ የጠቆሙት።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መላው ሕዝብ እና ልሂቃን ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ሦስተኛ፥ ለሕዝብ የቀረበ እና ለሕግ የታመነ አስተዳደር ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን እውን ለማድረግ መንግሥት የአስተዳደር ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር፣ እንዲሁም ተመሳሳይ እና ተጓዳኝ ዘርፎችን በማሰባሰብ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል ነው ያሉት።
መልካም አስተዳደር የዘመናዊ አስትዳደር የመሠረት ድንጋይ መሆኑን ይገነዘባል ሲሉም ገልጸዋል።
የሕዝብ አገልግሎት ለማዘመን በ2025ቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትልም መሠረት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይም በ2030 ዲጂታል ስትራቴጂ ይህንን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሠራ ነው ያብራሩት።
የመንግሥት ተቋማት የብዝኃነት ማዕከል እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ለኅብረተሰቡ የቀረበ እና እንግልትን የሚቀንስ የአገልግሎት ሥርዓትን ለመዘርጋት የተጀመረው እና ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ዲጂታል ማዕከል ለመስጠት ያለመው የመሶብ አገልግሎት ተጠናክሮ እና ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የመረጃ አሰባሰብ እና ትንተና አቅምን በላቁ ቴክኖሎጂዎች በማዘመን በመረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ አፈፃፀምን በማጎልበት የመረጃ ሉዓላዊ አቅማችንንም እንገነባለን ብለዋል።
አራተኛ፥ መንግሥት የዜጎችን ዋስትና የሚያስጠብቅ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት በ2018 በጀት ዓመት በትጋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
መንግሥት የሕግ አስከባሪ እና የፍትሕ ተቋማትን ለማሻሻል ሰፊ ርቀት መጓዙን ጠቁመው፣ የሕግ እና የአሠራር ማነቆዎችን በመፍታት እና ተቋማትን በነፃነት በማደራጀት የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎችንም አከናውኗል ብለዋል።
የተሻሻሉት የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ሕጎች በቴክኖሎጂም እንዲታገዙ መደረጋቸውን አንሥተው፣ የፍርድ ቤት አገልግሎትን ለማዘመን የተጀመሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራዎችን “ማስፋት፣ ማሟላት እና ማብቃት’’ የሚለው መርሕ ተግባራዊ ያደርጋል” ብለዋል።
በዮናስ በድሉ