የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ አራቱን የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።
የመጀመሪያው ትኩረት ዜጋን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታየ ጠቅሰው፤ የዜጎችን ደኅንነት እና ክብርን ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ሕገ-ወጥ ፍልሰትን በመቆጣጠር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ መብታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ዋና ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሌላው የትኩረት አቅጣጫ በዓባይ እና ቀይ ባሕር ላይ ያተኮሩ ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ጥረቶችን ማጠናከር መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓባይ እና ቀይ ባሕር ላይ ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያስቀድም ጠቁመዋል።
በዓባይ እና ቀይ ባሕር መካከል የምትገኘዋ ኢትዮጵያ እጣ ፋንታዋ እና መፃኢ ዕድሏ ከሁለቱ ውኃዎች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ፍትሕን ባልተከተለ አሠራር ተገልላ መቆየቷ ትክክለኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይ ግን ኢትዮጵያ በዓባይ እና ቀይ ባሕር ላይ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነቷን እንድታረጋግጥ መንግሥት በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ የባሕር በር ጉዳይን ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ሀሳብ ማድረግ መቻሉን አአንስተው፤ የቀጣናውን በጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብር እና ትስስርን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ ጥረቶች ይቀጥላሉ ብለዋል።
‘ቅድሚያ ለጎረቤት’ የሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን አጠናክሮ መቀጠል ሌላው የመንግሥት ትኩረት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ በዚሁ መርህ መሰረትም ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዘርፈ ብዙ ትብብር ለማድረግ ጥረት መደረጉን አውስተዋል።
በቀጣይነትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያጎለብቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና የንግድ ልውውጥ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ይደረጋል ብለዋል።
አራተኛው የመንግሥት ትኩረት በዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፎች ውስጥ ሚዛንን በመጠበቅ፣ በትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን እና ማስፋት እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ ያወሱት።
መንግሥት በዓለም መድረኮች የኢትዮጵያ ተሳትፎ እና ተደማጭነት እንዲያድግ፣ ተጠቃሚነቷም እንዲጎለብት፣ በዓለም ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና እንዲኖራት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ለዚህም አስፈላጊው ተቋማዊ ግንባታ እና የፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው ፕሬዚዳንት ታየ የጠቆሙት።
በቢታንያ ሲሳይ
#ebcdotstream #ethiopia #foriegnpolicy #redsea #abbay #ዓባይ