ለሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፥ መንግሥት እየተከተለው ባለው ብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ለሆነው ቱሪዝም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በዚህም ነባሮቹን የቱሪዝም መስሕቦች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ እንደሚደረጉ ጠቅሰዋል።
የኅብረተሰቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቶችን መንደፍ እና መተግበር፣ የማኅበረሰቡን ወግ እና ታሪክ የሚያሳዩ የባህል ማዕከላትን አብሮ መገንባት ዘርፉን ለማሳደግ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ነው ብለዋል።
"የቱሪዝም መዳረሻዎቻችንን በማልማት፣ መሰረተ ልማት በማሻሻል፣ የቱሪዝም አገልግሎት ጥራት በማሳደግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሰፊ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል መንግሥት ያምናል" ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ።
በዘርፉ በተከናወነው ሥራ ለጋራ ብልፅግና የሚውል ዕምቅ ዐቅም በተጨባጭ ለማውጣት መቻሉን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት የተዋበች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማብዛት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎቹን ከአየር ትራንስፖርት ጋር ጭምር በማስተሳሰር ለጎብኝዎች ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎችም ምቹ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ
#ebcdotstream #ethiopia #parliament #tourism #landoforigins