Search

የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅ ዘመናዊና ጠንካራ ሠራዊት ተገንብቷል - ጄኔራል አበባው ታደሰ

ማክሰኞ መስከረም 27, 2018 190

በኢትዮጵያ የተገነባው ዘመናዊና ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት የሀገርን ክብርን እና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መልኩ የሚጠብቅ መሆኑን የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ 21ኛ ጉና ክፍለ ጦር 30ኛ የምስረታ በዓል በኦሮሚያ ክልል ባቱ ከፍተኛ ወታዳራዊ መኮንኖች፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና ሌሎችም ታዳሚዎች በተገኙበት ተከብሯል።
በዚሁ ሁነት ላይ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በብቃትና ጀግንነቱ ጭምር የኢትዮጵያ አስተማማኝ አለኝታ መሆኑን ገልጸዋል።
የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ከንቱ ህልሞች በማምከን ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷ ተከብሮ እንድትዘልቅ ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
 
የደቡብ ዕዝ 21ኛ ጉና ክፍለ ጦር ባለፉት 30 ዓመታት ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በርካታ ወታደራዊ መሪ ያፈራና ትምህርታዊ ልምድ የተወሰደበት የሠራዊት ክፍል መሆኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ፥ ክፍለ ጦሩ የፀረ ሰላም ሃይሎችን የሽብር እንቅስቃሴ በማክሸፍ አኩሪ ገድል በመፈፀም ሀገርን በማፅናት በኩል የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል።
ክፍለ ጦሩ የተለያዩ ክፍለ ጦሮች እንዲመሰረቱ ልምድና መሰረት በመሆን እያገለገለ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ገልጿል።
የባቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመዲን እስማኤል በበኩላቸው ፤ የከተማዋና አካባቢው ሕብረተሰብ የኢትዮጵያ ጥንካሬ መገለጫ ከሆነው የሀገር መከላከያ ጎን ነው ብለዋል።
የአካባቢው ሕብረተሰብ ሰላምን በማፅናት ልማትና ዕድገቱን በተሻለ ደረጃ እያስቀጠለ ነው ያሉት ከንቲባው፥ ባቱና የአካባቢዋ ማኅበረሰብ ከሀገር መከላከያና ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ሰላምን በማረጋገጥ የበኩላቸውን እንደተወጡ ይገኛል ብለዋል።