የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በግድቡ ግንባታ ሂደት አበርክቶ ለነበራቸው ተቋማትና ግለሰቦች እውቅናና የምስጋና ፕሮግራም አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ፤ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የአፍሪካ አህጉርን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር አጀንዳ 2063 ዕቅድን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በርካታ ችግሮች ቢኖሩብንም በትብብርና በሕብረት ከተነሳን የተፈጥሮ ሀብታችንን ተጠቅመን ከመልማትና የብርሃን ምንጭ ከመሆን የሚያግደን ነገር አለመኖሩን በተግባር ለሁሉም ያሳየ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው በማለትም ገልጸውታል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር ግብርናን በማዘመን፣ ቱሪዝምን ከማስፋፋት ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ አቅምንና ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት አስችሏልም ነው ያሉት፡፡
ተቋሙ የኃይል ተደራሽነት ሽፋኑን ለማሳደግ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እና በየዓመቱ እያደገ የሚገኘውን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡
በግንባታው ወቅት አሻራቸውን ላሳረፉ ኢትዮጵያውያን ምስጋና ያቀረቡት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደትን በቅርበት በመደገፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የምስክር ወረቀትና የሜዳሊያ ሽልማት አበርክተዋል፡፡
በመሃሪ ዓለሙ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD