Search

ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘው አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር ይፋ ሆነ

ረቡዕ መስከረም 28, 2018 146

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘውን አዲሱን የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር ይፋ አድርጓል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ይህንኑ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ሚኒስቴሩ አዲስ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶች እና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 ማዘጋጀቱን እና በዚሁ መሠረትም የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር በአዲስ እንደሚተካ ገልጸዋል።
በሥራ ላይ ያለው ሰሌዳ ከዘርፉ ዕድገት እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ማስፈለጉን ነው ያመላከቱት።
ነባሩ ሰሌዳ ለቁጥጥር ሥርዓትም አመቺ አለመሆኑን እና ለሕገወጥነት የተጋለጠ መሆኑን ገልጸው፣ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሠራር የሚመራ በመሆኑ ለአሠራር አመቺ ነው ብለዋል።
አዲሱ ሰሌዳ ስለተሽከርካሪው ሙሉ መረጃ የሚሰጡ እና ተቆጣጣሪ አካላት በቴክኖሎጂ የሚለዩዋቸው ምሥጢራዊ መረጃዎችን ያካተተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ማጭበርበርን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም አዲሱን የተሽከርካሪ ሰሌዳ ሙሉ በሙሉ የመተካት ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸው፣ የተሽከርካሪ ባለቤቶች በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምዝገባ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።