ስኬቶችን እያስመዘገበች ለቀጠለችው ኢትዮጵያ የሚመጥን ጠንካራ ሠራዊት መገንባቱን የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።
የኢትዮጵያን ክብር እና ሉዓላዊነት በላቀ ብቃት እና ዝግጁነት የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ ክብር እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቆ መዝለቅ የዚህ ትውልድ አደራ እንደሆነ አንሥዋል።
ሌተናል ጄኔራሉ በየደረጃው ካሉ የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖች እና ኃላፊዎች ጋር በመምከር በግዳጅ አፈጻጸም ቀጣይ ተልዕኮዎችን በተመለከተ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ ከጥንት ጀምሮ አብሮ የዘለቀ እና አሁንም በላቀ መልኩ የቀጠለ መሆኑን አንስተው፣ የሠራዊቱ ጀግንነት፣ ግዳጅ እና ተልዕኮ የመፈፀም ብቃት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የቀደሙት አያቶች በአኩሪ የጀግንነት ገድል ከነ ሙሉ ክብሯ ያስረከቡንን ሀገር እኛም በላቀ ክብር እና ሞገስ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግደታ አለብን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለጠላት አስፈሪ እና ለሀገር አኩሪ የሆነ ጠንካራ እና ዘመናዊ ሠራዊት መገንባቱን አንሥተው፤ በዚህ ረገድ የምሥራቅ ዕዝ የሀገርን ክብር እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ለላቀ ሀገራዊ ተልዕኮ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ቡድን በክህደት የጠላት ተልዕኮ ለማስፈፀም ቢሞክርም በዕዙ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።
የምሥራቅ ዕዝ በዚሁ የግዳጅ አፈፃፀም ፅንፈኛ ቡድኑን በመከታተል እርምጃውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ወታደራዊ እርምጃው የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

ዋና አዛዡ እንዳመለከቱት፣ ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃይል ጋር በመጣመር የሚደረጉት ስምሪቶች ውጤት ማምጣታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ራሱን ችሎ በመንቀሳቀስ አኩሪ ግዳጅ እየፈፀመ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ቡድን የኢትዮጵያን ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል ሀገር እና ሕዝብን እየወጋ መሆኑን ሕዝቡ በአግባቡ በመረዳቱ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም አጋርነቱን እያሳየ እንደሆነ እና ሠራዊቱም ተከታትሎ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምሥራቅ ዕዝ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር እና የጎጃም ዞኖች በመንቀሳቀስ በፅንፈኛ ቡድኑ ላይ ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።