Search

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማንንም የማይጎዳ ፕሮጀክት ነው፡- ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ

ረቡዕ መስከረም 28, 2018 368

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማንንም የማይጎዳ ፕሮጀክት መሆኑን የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሼክ ሀሰን ሙሐመድ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከአል-ዓረቢያ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአካባቢው የኃይል ምንጭ የሚሆን ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ የተገነባበት አካባቢ የእርሻ ቦታ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ምክንያት የሚያስቀረው ውኃ እንደማይኖር ጠቅሰዋል።
ከ5 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው ግድቡ፣ በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ እንደምታቀርብ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ሶማሊያም በቀጣይ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ጠቁመው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማንኛውም ልማት በጣም አስፈላጊው እና ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ገልጸዋል።
ግድቡ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ትጋት በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ስለያዘችው አቋም ላይ ሶማሊያ ስላላት አስተያየት የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከ2 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ልማት እንደሚያስደስታቸው ነው የተናገሩት።
ግድቡ ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር የሚያቃቅር ነገር እንደሌለው ጠቅሰው፤ ሦሰትቱም ሀገራት በጉዳዩ ላይ የጋራ አቋም እንዲይዙ ለማገዝ በበኩላቸው ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር በግድቡ ጉዳይ እንድትስማማ ሀገራቸው የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ጠቅሰው፣ በንግግር መግባባት እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደነገሯቸው ጠቁመዋል፡፡
በለሚ ታደሰ