ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት የ‘ግሎባል ጌትዌይ’ አጋርነት ስምምነት በመፈራረም የረጅም ጊዜ ወዳጅነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረዋል።
ስምምነቱን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ተፈራርመዋል።
የ‘ግሎባል ጌትዌይ’ አጋርነት የዲጂታላይዜሽን፣ ታዳሽ ኃይል፣ የግብርና ምርት ሰንሰለት ሥርዓት (agri-food systems) ፣ ጤና፣ ዘላቂ መሠረተ ልማት እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነትን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ላይ ትብብር እና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
ሁለቱ መሪዎች ከፊርማው በፊት፣ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነትን ማጠናከር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያላቸውን ትብብር ማስፋት ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ይህ ስምምነት የጋራ ስትራቴጂካዊ ራዕይን ለመቅረፅ እና በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል የበለጠ የማይበገር አጋርነት ለመፍጠር ወቅቱን የጠበቀ ስምምነት ነው።
የዚህ ስምምነት መፈረም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ወሳኝ እርምጃ መሆኑም ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል በ2016 የተደረሰውን የስትራቴጂካዊ ተሳትፎ የጋራ ስምምነትንም ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርስም ነው የተገለጸው።