Search

የመደመር ፍልስፍና አመራር ውጤት የሆነው የሕዳሴ ስኬት በፕሮፌሰር ሳሊም አሊ ብዕር ሲገለጽ

ሓሙስ መስከረም 29, 2018 1236

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በታዋቂው ፎርብስ መጽሔት ላይ ላይ ሰፊ ሀተታ ያወጡት አሜሪካ በሚገኘው ደላዌር ዩኒቨርሲቲ ሊቀመንበር እና የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሊም አሊ፥ "ግድቡ የተቀናጀ አመራር የታየበት ውጤታማ ፕሮጀክት ነው" ብለውታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአፍሪካ ትልቅ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማስመረቅ አስደናቂ ስኬት አስመዝግቧል ይላሉ ሀተታቸውን ሲጀምሩ ፕሮፌሰር ሳሊም አሊ።

"የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ባደረጉት ጫና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ለጋሽ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ የነፈጉት ግድብ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ርብርብ በድል ተጠናቅቋል" በማለት ነው ኢትዮጵያውያን ግድቡን እንዴት ስኬታማ እንዳደረጉት ያወሱት።

ግብፅ በፕሮጀክቱ ላይ እንቅፋት ለመሆን መጣሯን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰሩ፥ የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የሚመሩት መንግሥት ግን በጽናት ፕሮጀክቱን ማጠናቀቁን አስታውሰዋል።

በግድቡ ጉዳይ ሁሉም ፊቱን ሲያዞር ኢትዮጵያውያን ግን እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ ራሳቸው የገንዘብ ምንጭ በመሆን ይህን ስኬት ማስመዝገባቸውንም ያትታሉ በጽሑፋቸው።

ኢትዮጵያውያን በቦንድ ግዢ፣ በዘመቻ፣ በስፖርታዊ ዝግጅቶች፣ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ንቅናቄ እና የተለያዩ የዕጣ ሽልማቶችን በማዘጋጀት ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ ያሳዩት ኅበረት የሚደንቅ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር አሊ።

የግድቡ በስኬት መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማያገኘው ከግማሽ በላይ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሩህ ተስፋን እንደፈነጠቀም በጽሑፋቸው ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) ለዚህ ግድብ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ እንደነበርም ነው ፕሮፌሰሩ ያወሱት።

በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከመሰረቱ ማንቀሳቀስ ባይቻል ኖሮ፤ ግድቡን ከፍጻሜው ማድረስ ከባድ እንደነበርም አስታውሰዋል ጸሐፊው።

ግድቡ የአመራር ቅብብሎሽ ውጤት መሆኑንም ጠቅሰ ይህ ዓይነቱ ግድቡ ስኬታማ የሆነበት አመራር ውጤታማ የሚሆነው አጀንዳውን የጋራ በማድረግ፤ ኅብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ሲቻል እንደሆነ የራሳቸውን ልምድ አክለው ጽፈዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ወደ ሕዝብ በመውረድ እና በማስተባበር ፕሮጀክቱን የጋራ አጀንዳ የሚያደርጉበት አካሄድ መከተሉን ያወሱት ጸሐፊው፣ ግድቡ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረገው እንዲህ ዓይነቱ አሳታፊ አመራር እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የተያዙ ታላላቅ የግል ድርጅቶችም ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ስኬታማ የመንግሥት ተቋማትም ለግንባታው የድርሻቸውን መወጣታቸው ሌላው የግድቡ ስኬት ምስጢር እንደሆነ ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) የኖቤል ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር ትብብር እና ውህደትን ማዕከል ባደረገው "መደመር" ፍልስፍና እንደሚመሩ መጥቀሳቸውን የሚያስታውሱት ጸሐፊው፣ የሕዳሴ ስኬትም ከዚሁ የአመራር ፍልስፍናቸው እንደመነጨ ጠቅሰዋል።

ሕዳሴ ሀገሪቱ አሁን የጀመረችውን የዘላቂ ልማት እንቅስቃሴ እና የቀጣናው የኃይል ሚዛን ለመሆን ያየዘችውን ዓላማ ለማሳካት አቅም እንዳላት ማሳያ እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።

ግድቡ በዋነኛነት የተሠራው ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሆኑ የሥነ-ምህዳር ተጽዕኖውን አነስተኛ ያደርገዋል የሚሉት ፕሮፌሰር አሊ፥ ይህ ደግሞ የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ያላቸውን የውኃ እጥረት ስጋት በማቃለል ቀጣናዊ መረጋጋትን እንደሚፈጥር ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኮሚሽን እና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ በኃይል እና በውኃ አቅርቦት ረገድ ትብብርን እንድታስቀድም ተጨማሪ ኃላፊነት እንደሰጣት ጠቁመዋል።

በለሚ ታደሰ