የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ እና ብቁ ሠራዊት በማፍራት ሀገራዊ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። 

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ በአየር ኃይል አካዳሚ መሠረታዊ ውትድርና ሙያ የሰለጠኑ ምልምል ወታደሮችን የማስመረቅ ሥነ-ሥርዓት ባደረጉት ንግግር፣ "እኔ ለሀገሬ መሥዋዕት እሆናለሁ ብላችሁ ወደ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተቀላቀላችሁ ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል የመገንባት ውጥን ይዛ እየሠራች መሆኑን ገልጸው፣ አየር ኃይሉ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የያዘችውን ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል የመገንባት ውጥን የሚመጥን ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ማብቃት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።
ሀገር እያከናወነች ያለው የልማት ሥራ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን እየተደረገ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የሰው ኃይል በማጠናከር እና ዘመናዊ መሣሪያ በመታጠቅ ሠራዊቱ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ከፍታ የማይፈልጉ ሁለቱ ጠላቶች፣ የውጭ ጠላቶች እና የእነሱ ተላላኪዎች እና ጉዳይ አስፈፃሚዎች ናቸው ሲሉ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።