“በጥቂት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ ከርሃብ እና ከልመና ተላቅቀው ወደ ብልጽግና የገሠገሡ ሀገራት ታሪክ የሚነግረን ነገር ቢኖር፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብልጽግና ለማምራት የሚቻልባቸው፣ተሞክረው አዋጭ የሆኑ፣ ወይም አዳዲስ አቋራጭ የዝላይ መንገዶች መኖራቸውን ነው''
********************
ከዓለማችን የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ከዐሥርት ዓመታት በፊት ሕዝቧን ለመመገብ እስኪሳናት ድረስ በድህነት አዘቅት ውስጥ የምትዳክር ሀገር ነበረች።
በተለይ በ1960ዎቹ አጋማሽ አብዛኛው የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ የቀን ተቀን ኑሮው የተመሠረተው በዕርዳታ በሚገኝ እህል ሲሆን የሀገሪቱ ኢኮኖሚም በውጭ መንግሥታት በተለይም በአሜሪካ መንግሥት ከሚገኝ የቀጥታ ድጎማ ላይ የተመሠረተ ነበር።
በወቅቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት የፈጠረው በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ አጥ ዜጋ በነበራት ደቡብ ኮሪያ የሕዝቧ የነብስ ወከፍ ገቢ የዓለማችን ድሀ አገራት ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል የሚገኝ ነበር።
ሆኖም ፕሬዚዳንት ፓርክ ቹንግ ሄይ ወደ መሪነት ሲመጡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከሥር መሠረቱ ለመቀየር የሚያስችሉ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕቅዶች ተነድፈው በተግባር መዋል ጀመሩ።
ደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚዋን ለመቀየር በጠንካራ የመንግሥት ፖሊሲ እና በሕዝቦቿ ታታሪነት ወደብልጽግና የምታደርገውን ሽግግር አነስተኛ ኢንደስትሪዎችን በማቋቋም ነው የጀመረችው።
በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ የምናየውምይህንኑ ነው። በመጽሐፉ ገጽ 91 ላይ የሚገኘው ፍሬ ሐሳብ በትክክል እንደሚያሰምርበት “በጥቂት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ከርሃብ እና ከልመና ተላቅቀው ወደ ብልጽግና የገሠገሡ ሀገራት ታሪክ የሚነግረን ነገር ቢኖር፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብልጽግና ለማምራት የሚቻልባቸው፣ ተሞክረው አዋጭ የሆኑ፣ ወይም አዳዲስ አቋራጭ የዝላይ መንገዶች መኖራቸውን ነው'' ይላል።
ይህ ሐሳብ ኢትዮጵያውያንም ውጤታማ በሆኑ አዋጭ መንገዶች ወይም አቋራጭ የዝላይ መንገዶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማፋጠን የሚጠቅሙ መፍትሔ አዘል እውቀቶች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያሳስብ የዕድገት መመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ለዚህ አንቀፅ እንደምሳሌ ያነሣናት ደቡብ ኮሪያም ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ በውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ የነበረውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመቀየር የሞከረችበት መንገድ በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው በተግባር ተሞክሮ “አዋጭ” ሆኖ በመገኘቱ ለዘመናት የነበረውን የድህነት ታሪክ መቀየር ችላለች።
በተግባር ተሞክሮ አዋጭ በሆነ የእመርታ ጅማሮ ስኬታማ የሆነችው ደቡብ ኮሪያ ኢንደስትሪዎቿን አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ በሚል ደረጃ በደረጃ በማሳደግ እና በማስፋፋት ዛሬ ላይ ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት የነበረው የሀገሪቱን የኢኮኖሚመቀየር ችላለች። ከዓመታት በፊት አንድ መቶ የአሜሪካ ዶላር የነበረውን የሕዝቦቿን አማካኝ ገቢ አሁን ወደ 35 ሺህ ዶላር ማሳደግ ችላለች።
መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመቀየር የነደፈውን ፖሊሲ መርሕ በማድረግ በሕዝቦቿ ታታሪነት በዓለም ላይ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው ሀገራት በ13ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝም አስችሏል።
እዚህ ላይ በደቡብ ኮሪያ የሀገሪቱን ሁኔታ እና የሕዝቡን ኑሮ ለመቀየር
በመንግሥት የተነደፈው ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቧ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነበር።
ይህንን ሐሳብ በተመለከተ በመደመር
መንግሥት መጽሐፍ ላይ ቀጣዩን ሐሳብ እናገኛለን።
“ለአንድ ሀገር መጥፊያዋም መዳኛዋም ሕዝቧ ነው። ሕዝቧ የነገን ተስፋዋን ያለመልማል ወይም የማዘግየት ሚና ይጫወታል። ሕዝብ ተምሮ እና ነቅቶ ለአንድ ዓላማ ከተሰለፈ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ዐቅም ነው። የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ለዚህ ምስክር ናቸው።” (የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 53)
እንዲህ ያለውን የይቻላል ተስፋ በተግባር ላየ እና ላወቀ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ከዛን ጊዜው የደቡብ ኮሪያ እጅግ የተሻለ መሆኗን ለተረዳ፣ ነገ በእርግጠኝነት የሚጨበጥ ተስፋ እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ማስረጃ አይፈልግም። ይልቁንም በእርግጠኝነት ለዚህ ዓላማ ይሰለፋል። ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ጸጋ ደግሞ ይህን የሚጨበጥ ተስፋ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስጦታዎች ናቸው። ይህንንም የመደመር መጽሐፍ ሲያስቀምጠው፦
“...የቤት ሥራችንን የሚያቀልሉ፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ፣ በተለያየ መንገድ ልንጠቀማቸው የምንችላቸው ሰፊ ዕምቅ ሀብቶች ባለቤቶች መሆናችንን ዓይናችንን ገልጠን ማየት አለብን። መንገዳችንን ቀይረን ራሳችንን እና ሀገራችንን በአዲስ መንገድ እና ትልም መምራት ያስፈልጋል።” - (ገጽ 54)
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የመጣችበትን “እየደመሰሱ የመቅዳት” ረጅም ጉዞ ቆም ብሎ በማየት እና በመመርመር ስለነገው ጉዞ ማሰብ ይገባል የሚለው።
እናም አሁን ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ የነደፈችው ፎኖት በእርግጥም እንደ ደቡብ ኮሪያ ከዓለም ኃያላን ተርታ ለመሰለፍ ያላትን ርዕይ እና ይህንን ሕልም እውን ለማድረግ የመረጠችው ስልት ግልጽ መሆኑን ነው።
በዋሲሁን ተስፋዬ