የእስራኤል መንግሥት ካቢኔ ከሃማስ ጋር የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ማፅደቁን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ዛሬ ማለዳ የእስራኤል ካቢኔ ያፀደቀው የሰላም ስምምነት በጋዛ በ24 ሰዓታት ውስጥ ጦርነቱ ቆሞ፤ የተያዙት እስራኤላውያን ምርኮኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲፈቱ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የታወጀው ትላንት ሲሆን፣ በስምምነቱ መሰረት በጋዛ የተያዙ እስራኤላውያን እና በእስራኤል እስር ቤቶች ያሉ ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁ ይሆናል ሲሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ያቀረቡት ባለ 20 ነጥብ እቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው ስምምነቱ እስራኤል ወታደሮቿን ከግጭት ቀጣናው ወደኋላ እንድትመልስ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል።
በለሚ ታደሰ